በአሜሪካ እና በአውሮፓ ለምትገኙ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ ማህበራት ፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች

በአሜሪካ እና በአውሮፓ ለምትገኙ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ ማህበራት ፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች

እኛ ትላንትና ዛሬም ወደፊትም ለህባችንና ለሀገራችን የገባነውን ቃል ለሠከንድም አናጥፍም:: ትግሉም ይህንን ቆራጥነት የሚጠይቅ መሆኑን ለናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል:: በህዝባችን እና በሀገራችን ላይ የተጫነው ሥርዓት የህዝባችንን ህልውና የሀገራችንን አንድነት ከድጡ ወደ ማጡ እየወሰደው ይገኛል::

የኛ ትግል እስከዛሬ ካሳለፍነው ቢከብድ እንጂ ያንሳል ብለን አናምንም:: ሥርዓቱ መኢአድን እና አባላቱን እንዲሁም ደጋፊዎች ለመጥፋት ያልቆፈረው ጉድጓድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም:: የመኢአድ አላማ ግን በማያጠራጥር መልኩ በሁሉም መልኩ እየጎመራ እና እያሸተ መሄዱ አይቀሬ ነው:: ነገር ግን አሁን የት ናችሁ ብላችሁ ከጠየቃችሁን በጠባቡ የዲሞክራሲ ሜዳ ዉስጥ ቆመን ስለህዝባችን እየተሟገትን ነዉ:: ትግሉ በያንዳንዳችን ያላማ ፅናት ፣ የሀገር ፍቅር የሚወሰን ይሆናል:: እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ሁሉንም የግፍ አይነቶች ሥርዓቱ ፈፅሞብናል:: ይህ በመሆኑ ተስፋ አንቆርጥም:: ግፍና መከራዉም ትግሉን አያስተጓጉለዉም:: በማያወላውል መልኩ ከዳር ይደርሳል::

የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነትና የዲሞክራሲ ፍላጎት ጠንካራ ነዉና እኛም ይሄን የህዝብ ፍላጎት ግብ ለማድረስ ቆርጠናል እና ብዙ መዉደቅና መነሳት አለብን:: መውደቅ መነሳታችን ግን አንዱ የትግል መለኪያ ሥለሆነ ደጋፊዎቻችን ሥንወድቅም ሆነ ሥንነሳ አብረውን የመስዋዕትነቱ ተካፋይ ሆነው እንዲቀጥሉ እና የገቡትንም ቃል እንዲያከብሩ መተሳሰባችን እና መተሳሰራችን መቀጠል እንዳለበት ሁልየም ቢሆን በኛ አእምሮ ውስጥ አለ::

በናንተም በኩል ይኸው እንዲኖር እንፈልጋለን ፡፡

ዛሬ በመላ ሀገሪቱ እየተቀጣጠለ ያለው የነፃነት ጥያቄ የመኢአድ መሠረት ይዞት የተነሳው የሀገር እና የህዝብ ፍቅር መሆኑን ታጡታላቸሁ የሚል እምነት የለንም:: ይህ ማለት መኢአድ የሌለበት ትግል እንደሌለ አስረግጠን መናገር እንፈልጋለን:: እናንተም ድርጅታችሁ መኢአድ በፅናት ካደራጃቸው እና ካሣደጋቸው ልጆቹ ጋር አብራችሁ እንደበፊቱ መቀጠል አላማችሁ ታደርጉ ዘንድ እናሳስባለን ፡፡

የሚነፍሰው የአሉባልታ ንፋስ እንዲሁም አንባገነኖች መኢአድን አፈረስነዉ እያሉ የሚደነፉት ድንፋታ እንደማያታልላችሁ እና ከደጋፊነታችሁ እንደማያዘናጋችሁ እናዉቃለን:: ሆኖም አበው እንደሚሉት ጦር ከፈታው ወሬ የፈታዉ ነው እና ለወሬው እና ለአሉባልታው ወሬ ቁብ ነገር ባለመስጠት የመኢአድ ቆራጥ ልጆቻችሁን ቆራጥ ተጋድሎ ዋጋ በመስጠት አብራችሁን መሆናችሁን የምንፈልገው መሆኑን እናስገነዝባለን፡፡ በአሁኑ ሰአት የአምባገነኖች ድብቅ መሳሪያ የሆነዉን አበባው መሃሪን እና ከርሱ ጋር ያሉ ጥቂት አድር ባዮችን መላዉ የመኢአድ አባላት: ደጋፊዎች እና የኢትዮጵያ ህዝብ መዉጫ መግቢያ እያሳጧቸዉ ነዉ:: በህዝብ የተተፋዉ አበባዉና ከሀዲ ቡድኑም በህዝብ መውጫ መግቢያ ስላጣ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን መኢአድን ለአቶ ማሙሸት አመራር ላስረክብ ነዉ እያሉ በውጭ ሀገር የምትኖሩ አንዳንድ ሠዎችን ማደናበራቸው አልቀረም:: አበባውን አሁን አገሪቷን በአንባገነነት አንቆ ከያዛት ስርኣት መለየት አይቻልምና አበባዉ የሚነዛዉን ማንኛዉንም ሀሰት ማመን መታለል መሆኑን በአንክሮ እንገልጻለን::

አባቶቻችን ለሀገር እና ለህዝብ የከፈሉት ትልቅ ዋጋ እንዳለ ሆኖ መቻቻል በሚሉት የፍትህ እንቅፋት ባንዳዎችን በመሸከም ብዙ አርበኞችን በመግፋት የሀገር ፍቅር እና የህዝብ ሥሜት እንደተኮላሸ እና የኛ ትውልድ እንደመከነ በናንተ ዘንድ አይታወቅም የሚል እምነት የለንም:: በመሆኑ የኛ ትግል ከጠቅላላ ጉባኤዉም በላይ የባንዳዎችን ቅስም ለአንዴና እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሠብር ሆኖ በህዝብ ትግል ይደመደማል እንጅ ” ከብረት ምሰሶ ከወንድ አንተን አየሁ የወንዶቹ ባል ፈለቀ እጅግ አየሁ ” የተባለላቸው አርበኞች እያሉ ባንዳ በነሱ ላይ ተሾሞ በነሱ ላይ ግፍ ሲፈፅም እንደነበረ ሁሉ ለአበባው እና መሠሎቹ ጆሮ መሥጠት ይህንን ታሪክ መድገም ነው፡፡

አበባዉ አሁን በዉጭ ያለዉን ሀይል ለማደናበር እና የባንዳ ስራዉን ለማራመድ እንዲመቸዉ ብሎም ደጋፊዎችን ግራ ለማጋባት ስላለመ ጠቅላላ ጉባዔ አድርገን መኢአድን ልናስረክብ ነዉ እያለ ነዉ:: በኛ በኩል ለአንድየ እና ለመጨረሻ ጊዜ የአበባውን ጉዳይ በደንብ እንድትረዱት እናሳስባለን:: አበባዉን እያንዳንዱ አላማዉን ጠንቅቀን ስለምናዉቅ ነዉ ከዝንብ ማር እንደማይጠበቅ ሁሉ ከአበባዉም ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም:: ከአበባው ጋር መስራት ይቻላል ብሎ ማሰብ ማለት ከወያኔ ጋር መስራት ይቻላል ማለት ነዉ:: ወያኔ ለአበባዉ የመኢአድን ቢሮ ነጥቆ ያስረከበዉ መኢአድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አንቆ ለመግደል ከአበባዉ የተሻለ ጥሩ መሳሪያ እንደሌለዉ ስለተረዳ ነዉ:: ስለዚህ አበባዉ በሚያሰራጨዉ የሀሰትና የጥፋት መረጃ የተታለላችሁ አንዳንድ ደጋፊዎች እየደወላችሁ እንዳታስቸግሩን በአክብሮት እናሳስባለን::

የዲሞክራሲ ትግላችን ይቀጥላል:: በቅርቡ የዘመን እና የአብርሃም መፈታት ለትግላችን ጉልበት ጨምሮለታል:: የመአኢድ ም/ፕ ዘመነ ምህረት በኢሳት ሰሞኑን ቀርቦ በስፋት እንዳብራራዉ እኛ የመኢአድ አመራር እና አባላት እንታሰራለ እንጅ ልባችንን ከትግሉ ሜዳ ዉስጥ ማሰር አይችሉም:: ወያኔዎች ሞራላችንን ለመግደል ቢደበድቡን የትግል ሞራላችን የማይሰበር እና ጽኑዕ ነዉ:: ዘመነ ምህረቴ አጠንክሮ እንደገለጸዉ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል:: ዲሞክራሲ እና ሰበአዊነት ብሎም የበለጸገች ኢትዮጵያ እዉን እስክትሆን ድረስ እንታገላለን:: ትግላችን በማንም በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረት አይደልም:: ትግላችን የህዝባችንን ዲሞክራሲ እና ሰበአዊን መብት ከነጠቁ አንባገነኖች ጋር ነዉና ብዙ መከራ እና ስቃይ እንደሚኖርበት እሙን ነዉ::ግን ትግላችን በማንም በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አይደለም::

በተረፈ በያላችሁበት የመኢአድን አላማ ግብ ለማድረስ እንዳትሰለቹ: መኢአድንም ከመደገፍ ለቅጽበት እንዳታመነቱ እያሳሰብኩ የከበረ ሠላምታ ይድረሳችሁ እላለሁ ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !

ማሙሸት አማረ /የመኢአድ ፕሬዝዳንት

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.