የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ የጠባብነት ወይስ የዲሞክራሲ?

የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ የጠባብነት ወይስ የዲሞክራሲ?

የኦሮሞ ተማሪዎች የኦሮሚያ መሬት አለአግባብ በሌባ ባለሃብቶች: የህዝብ መሰረት በሌላቸዉ ተቋማት እና ህግን መሰረት ባላደረገ አካሄድ የሚከናወንበትን መቀራመት እየተቃወሙ ነዉ:: ወያኔ ይሄን ተቃዉሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምታቀርብበት ዘይቤ ደግሞ በሌላ መልክ ነዉ:: የኦነግን አላማ ለማሳካት የተነሱ ተማሪዎች ናቸዉ:: አዲስ አበባ አይስፋፋ የሚሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ኦሮሚያ የሚባለዉን አገር የመገንጠል ዕቅድ ስላላቸዉ ነዉ:: ስለዚህ ኦሮሞ ያልሆናችሁ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ከኔ ጎን ሆናችሁ ተማሪዎችን ተቃዎሙ እያለች ትቀሰቅሳለች:: መቼም ወያኔ ፕሮፖጋንዳ ላይ ጎበዝ ናት:: ሰዉ መከፋፈልም ላይ የሚችላት አልተገኘም::

ጥያቄዉ ግን ወያኔ ብቻዋን ሲያሰኛት ይሄ ቦታ የኦሮሞ ነዉ: ሳያሰኛት ደግሞ ይሄን ቦታ ነጥቄ ለኢትዮጵያ ሰጥቻለሁ:: ሸዋ የኦሮሞ ብቻ ነዉ:: ሌላ ጊዜ ደግሞ ሸዋ የኦሮሞ አይደለም:: ይሄኛዉ አካባቢ ደግሞ የአማራ ነዉ እያለች በኢትዮጵያ ምድር እንድታናፋ ማን ስልጣን ሰጣት:: የጨበጠቸዉ መሳሪያ ነዉ ይሄን ስልጣን የሰጣት የሚል መልስ የመለሰ ሰዉ መልሱን በትክክል አግኝቶታል::

የወያኔ የአስተሳሰብ ቅራኔና ተፋልሶ መቆሚያም ስለሌለዉ እራሷ ላይ እሳት እንዳነደደባት ይኖራል:: ወያኔ ስትፈልግ አዲስ አበባን የኦሮምያ ነዉ ትላለች:: በማግስቱ ብድግ ብላ ደግሞ የኢትዮጵያ ነዉ ትላለች:: ሲያሰኛት ደግሞ ብድግ ብላ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ነዉ ትላልች::

ወያኔ ሲትፈልግ ጎንደርን ሸንሽና ይሄኛዉ የቅማንት: ያኛዉ የወልቃይቶች : ከዚህ በመለስ ደግሞ የትግራይ ነዉ ትላለች:: ከ65 % በላይ አማሮች የሚኖሩንበትን ቤኒሻንጉልን ደግሞ ሲይሰኛት የአማራ ሀገር አይደለም:: አማራ ይዉጣ ትላለች: ደስ ሲላት ደግሞ አማራዉን ያባረሩት የክልሉ ባለስልጣናት ይታሰሩ በኒሻንጉልም የአማራ ነዉ እያለች ትቀልዳለች::

እንግዴህ ችግር የሚነሳዉ እዚህ አስተሳሰቧ ቀዳዳ ዉስጥ ለመግባት የሚቸገሩ ሰዎች ሲነሱ ነዉ:: ይሄ ሁሉ ቀልድ የማይስማማቸዉ እና እንዲህ አይነት ቀልድ ልክ አይደለም ብለዉ የሚቃወሟትን በሶስት ነገር ትወርድባቸዋለች:-
1ኛ/ በጥይት
2ኛ/ ስም በማጥፋት
3ኛ/ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ ጋር እንዲጋጩ በማድረግ
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የዚህ የተቃርኖ አስተሳሰብ ዉጤት ነዉ:: በመሰረቱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዋና ግቡ ድሃዉን ገበሬ ባዶ እጁን አስቀርቶ ለጥቂት ሌባ ጎሰኛ ባለሃብት ተብዬዎች መክበሪያ የሚሆን ሰፊ መሬት ማዘጋጀት እንደሆነ በርካታ መረጃ ማቅረብ ይቻላል:-

1ኛ/ማስተር ፕላኑ ሲዘጋጅ የሁሉም ተሳትፎ የሌለበት
2ኛ/ የሚፈናቀለዉ አርሶ አደር የሚሰጠዉ ካሳ እዚህ ግባ የማይባል ወይም ከነጭርሱ ካሳ የሚባል ነገር ሳይታሰብለት መሬቱን ተነጥቆ የሚባረር
3ኛ/ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ከተማን አንድ ጊዜ የኦሮሚያ ነዉ : ሌላ ጊዜ ደግሞ ኦሮሚያ እዚህ ከተማ ዉስጥ ምንም የለህም በማለት ነቅለህ ዉጣ የሚል አሳፋሪና ሌላዉን ወገን አዋራጅ ትዕዛዝ በመስጠት በኦሮሚያ ክልል ህዝብ ስነልቦና ላይ ጥባጥቤ የመጫወት ስራ ተሰሯል
4ኛ/ሌላዉን ኢትዮጵያዊ ሲያስፈራሩም ኦሮሞዎች አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ጋር ሊወስዱብህ ነዉ በማለት ወስላታ ፕሮፖጋንዳ ያናፍሳሉ

አሁን የኦሮሞ ተማሪዎች ብዙ ነገር ግልጽ ሆኖላቸዋል:: የኦሮሞ ልጆች ጥያቄ ፍንፍኔ የዚህ ወይ የዚያ የሚል ጉዳይ ብቻ አይመስለኝም:: የኦሮሞ ልጆች ጥያቄ እዉስጡ የታመቀ ብሶት አለበት:: ብሶቱ ደግሞ የተፈጠረዉ ወያኔ ኦሮሞ ህዝብ ላይ የምትቀልድበትን የስነልቦና የካርታ ጨዋታ ከመረዳት ነዉ::
ኦሮሞዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ መቆጣጠር እና ሀገሪቱ ላይ መልካም ሚና መጫዎት እንዳይችሉ ወያኔዎች ሆን ብለዉ ብዙ ደባና ተንኮል ይሰራሉ:: ኦሮሞዎች ከሌላዉ ኢትዮጵያ ጋር ይቃረኑ ዘንድ ወያኔዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም:: ወያኔዎች አሁንም የኦሮሞ ወጣቶች ያነሱትን ጥያቄ እዉነተኛ ገጽታ በማጣመም እና ሌላ ገጽታ እንዲያዝ በማድረግ የኦሮሞ ወጣቶችን ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ የመነጠል ስራ እየሰሩ ነዉ::

የኦሮሞ ወጣቶች ማንኛዉም አይነት ዲሞክራሲያዊ እና ሰበአዊ ጥያቄ ሊከበርና በተገቢዉ መልክ ሊፈታ ሲገባዉ ተማሪዎቹን በመግደል: በማሰር: በማሳደድ እና ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ እንዲነጠሉ ሁሉንም ክፉ የልዩነት ፕሮፖጋንዳዎች በማካሄድ ላይ ናቸዉ:: ኦሮሞዉ ላይ ጠባብ የሚል ፍረጃ ለጥፈዉ: አማራዉ ላይ ትምክህተኛ የሚል ፍረጃ ለጥፈዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ስነልቦና ጥባጥቤ ይጫወቱበታል::

ስለዚህ የኦሮሞ ልጆች ያነሱት ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ መሆኑን ኢትዮጵያዉያንን ሊገነዘቡ ይገባል:: ጥያቄአቸዉም የዲሞክራሲ የሰበአዊነት ብሎም ሀገራቸዉን የማስተዳደር የመመራት የመቆጣጠር ጥያቄ ነዉ:: ወያኔዎች ጎንደር ላይ እንዴት አንዱን መሬት የቅማንት ወይም የአማራ : እንዲሁም ያንኑ አንዱን መሬት የትግራይ ወይም የጎንደር እያሉ እማያመሱት እንዳለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እያስተዋለ ነዉ:: ይሄን የተቃወሙትን ደግሞ በጥይት እንዴት እየቆሏቸዉ እንደሆነ እያስተዋልን ነዉ::

የአማራ ህዝብ ከመላዉ ኢትዮጵያ ከሁሉም አቅጣጫ በወያኔዎች ትዕዛ ተነቅሎ እንዲጠፋ እየተደረገ እንዳለ እያስተዋልን ነዉ:: ወያኔዎች አማራ ከአንዱ አካባቢ በአንዱ ብሄረሰብ እንዲፈናቀል የሚያደርጉት ቅማንትን ወደዉ ወይም ግሙዙን ወደዉ አይደለም:: ወይም የቤኒሻንጉል ሰዎችን ወደዉ አይደለም:: ወይም ደግሞ የጉራፋርዳ ብሄረሰቦችን ወደዉም አይደለም:: ወያኔዎች ይሄን የሚያደርጉት የራሳቸዉ ሌባ ሀብታሞች መሬት የሚቆጣጠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ነዉ:: እንዲሁም አሁን የኦሮሚያ መሬትን ለመዝረፍ እና ለሌባ ባለስልጣኖቻቸዉ ለማከፋፈል ሲነሱ የአዲስ አበባ ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ይዘዉ መጡ::

ወያኔዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች የሚደርስባቸዉ መፈናቀል እና ከምድረ ገጽ በድህነት መጥፋት ጉዳያቸዉ አይደለም:: በአንድ የሶዮ ኢኮኖሚክስ ጥናት እንደተረጋገጠዉ ከአዲስ አበባ ዙሪያ በልማት: አበባ እርሻና ሌሎችም ጉዳዮች ስም የሚፈናቀለዉ አርሶ አደር ወደ መጨረሻዉ አዘቅት ዉስጥ ይገባል:: የመሬት ካሳ ተብሎ የሚሰጠዉ ገንዘብ ለወራት እንኳን አይበቃም:: የበርካታዉ አርሶ አደር ቤተሰብ ይበተና:: ጎዳና ላይ ይወድቃል:: በኤች አይቪ በሽታ ይሞታል:: እና እንግዲህ እንዲህ አይነት የወገናቸዉ ሰቆቃ የገባቸዉ የኦሮሞ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ የሰበአዊነት የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንጅ የጠባብነት ጥያቄ እንዳልሆነ ይታወቃል::

ወያኔ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዉያን ማስረከብ አለባት:: በዚህ ሂደት ዉስጥም ወያኔ እራሷ የአቅሟን ያህል የኢትዮጵያዊነት ድርሻዋን መጫወት ይገባታል እንጅ የሁሉ ነገር ፈጣሪና ሰሪ መሆን አልነበረባትም:: ሆኖም ወያኔ ሁሉንም እኔ ልዋጠዉ : ሁሉንም እኔ ልሰልቅጠዉ ስትል የጨበጠችዉ ሁሉ እንደ ጉም ከእጇ ትን ብሎ እንዳይጠፋባት የኢትዮጵያዉያንን የዲሞክራሲና የሰበአዊ መብት ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ይገባታል የሚል የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በባዛት ቢሰጣትም ጆሮ ያላት አትመስልም::

በአጠቃላይ የኦሮሞ ተማሪዎች የኦሮሚያ መሬት አለአግባብ በሌባ ባለሃብቶች: የህዝብ መሰረት በሌላቸዉ ተቋማት እና ህግን መሰረት ባላደረገ አካሄድ የሚከናወንበትን መቀራመት እየተቃወሙ ነዉ:: ይሄም የዲሞክራሲና የሰበአዊነት ጥያቄ እንጅ የጠባብነት ጥያቄ አይደለም::

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.