ገኖ ያልተሰማው የጎንደሩ ወህኒ ቤት እሳት ቃጠሎና አደጋው !

የማለዳ ወግ …ገኖ ያልተሰማው የጎንደሩ ወህኒ ቤት እሳት ቃጠሎና አደጋው !
=============================================
* የሟች መረጃ ድብብቆሽ በፋሲል ከተማ…
* በጎንደር 45 ሰው ሲሞት ህጻናትና አቅመ ደካሞች አሉበት
* ምርጫው አንድና አንድ ነው ፣ በእሳት ወይስ በጥይት
* በእሳትና በመትረየስ አፈሙዝ መካከል ፣ ሰቆቃ ወጎንደር

ዘረኝነት የነገሰበት ሶሻል ሚዲያ …
======================
የሶሻል ሚዲያው ፊስቡክና ትዊተር ሰሚነኛ መረጃ ግብአት ሊሰሙት በሚያም መረጃ የታጨቀ ነበር ። ያን ሰሞን የተራገበው ርሃብ እየከፋ መሆኑን የሚያስረዱ ተባራሪ መረጃዎች ፋታ ያልሰጠ ዘር ተኮር ሙግት ፣ ክርክርና እሰጣ ገባ ነግሷል ። ለዘር ነገር ሲነሳ የሚፈራው ሁሉ እንዳይሆን የሚጠብቅ ፈጣሪ መኖሩን ተስፋ ካላደረግን አካሔዳችን ደስ የሚል ሆኖ አላየሁትም ። አንዳንዴ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ፖለቲከኞች ተንኮለኞች ናቸው ፣ መሰሪ አላማቸውን ለማስረጽና የፖለቲካ አላማቸውን ለማስፈጸም አሰልጥነው የሚያሰማሯቸው የሶሻል ሚዲያውን ምሰለኔዎቻቸው በዘር ተኮር እሰጣ ገባ ነዋሪውን ማሰላቸቱን በርትተው ተያይዘውታል ። ጸረ ኢትዮጵያ ቡድኖች በህብረትና በፍቅር የኖረውን ዜጋ ወዳልተገባ ቀዳዳ እያድገቡ ብዙዎችን ማሰላቸቱ ተሳክቶላቸዋል ! ለዚህ ኢላማ መሳካት ዋና ኢላማቸው ታዋቂና ሀገር ወዳድ በሆኑት ላይ የተጠናከረ ዘር ቀመስ ስም ማጥፋት ዘመቻ መከዎን ነው ! ሰው ሶሻል ሚዲያው የሚያቀርበውን ፈጣን መረጃ ፋይዳ ቢስና ተጨባጭ ያልሆ ነው ለማስባል የሆነ ያልሆነውን ቀለም የሚቀቡ መሰሪዎች ሰራቸውን ተግተው እየሰሩ ለመሆኑ ብዙ ምልክቶች እያየን ነው ። እናም ለዘር ተኮሩ ከአንባጓሮ ያልተናነሰ እሰጣ ገባ ጀሮ ሰጥቸ ማላዘን አልሻም ። … የሰማሁት ያየሁትና የደረሰኝን መረጃ ሁሉ ከዘር ጋር ላቆራኝቸ ለመዘለባበዱ ነፍሴ ባይፈቅድም ገኖ ስላልተሰማው የጎንደሩ ወህኒ ቤት እሳት ቃጠሎና አደጋ ለመግቢያ የምለውን እላለሁ ። ቀጠል አድርጌም በአደጋው ባቻ ወደ ጎንደር ተጉዞ ስለ አደጋው ከተለያዩ ወገኖች መረጃ ያሰባሰበውን የጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋውን ” ሰቆቃ ወጎንደር ! ድንቅ ያልተሰማ መረጃ ልጋብዛችሁ ፈቅጃለሁ !

የሟች ድብብቆሹና በጎንደር …
====================
ሕዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም ለጎንደር ለጎንደሮች የከፋ ቀን ነበር ፣ ሀገሬው ባዕታ እስር ቤት እያለ የሚጠራው ወህኒ ተቃጥሎ በርካቶች የመሞት መቁስላቸው መረጃ ያደረሱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፣ በአደጋው የተጎዳ የለም ከሚለው ጀምረው የሟች ቁጥርን 17 አድርሰውት ተመልክተናል ። በሟችና በቆሰለው ዙሪያ የመረጃ ድብብቆሽ እንዳለና ከ25 በላይ የሞቱ እንዳሉ ብሰማም ዛሬ በገበያ ላይ የዋለው የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሙሉቀን በቦታው ሄዶ በማጣራት የሟች ቁጥር 45 መድረሱን መረጃ አቅርቧል ። ቁጥሩ ይህን ያህል አሻቅቦ በሟች ቁጥር ዙሪያ ከፍ ባለ ልዩነት መረጃ መደባበቁን ባልገምተውም የፋሲል ከተማ በወርሃ ህዳር በስጋት ስትናጥ መሰንበቷን መረጃዎች ደርሰውኝ ነበር …

በመንግስት ከተሰጠው መረጃ በጣም የሚለያየውን መረጃ ያቀረበልን ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው ዛሬው በሀገር ቤት ታትሞ በገበያ በዋለው ጋዜጣ በጎንደር ከሞቱት 45 ሰዎች መካከል ህጻናትና አቅመ ደካሞች እንደሚያካትት አሳዛኙን መርዶ እንደሚከተለው አቅርቦታል … !

ሰቆቃ ወጎንደር …
=============
የጎንደር ሕዝብ ዓመታዊውን የቅድስት ማርያም በአል ያከብራል። ምዕመኑ ከሎዛ ማርያም እስከ ግምጃ ቤት ማርያም ድረስ ባሉ የማርያም አብያተ ክርስቲያናት ሲነጉድ አርፍዷል። ጸአዳ በለበሰ ምዕመን ጎንደር ነጭ በነጭ ሆና አርፍዳለች። እከለ ቀን ሆነ፤ ካህናት ወደ ቅዳሴ ገቡ። በምሳ ሰዓት የታሰረ የሚጠይቀው ደግሞ ወደ በአታ ማረሚያ ቤት ሄደ። በግምት ከ7፡00 እስከ 7፡30
ቢሆን ነው። የሚጠይቁ ሰዎች ውስጥ እያሉ የማረሚያ ቤቱ ‹መንስ ቤት› (ምግብ የሚዘጋጅበት ቤት) ቃጠሎ ተነሳ። የጥበቃ ፖሊሶች ዝግጁ አልነበሩም። በከተማው በቂ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪና የለም፤ ከአየር ማረፊያ የመጣውም ቢሆን አደጋውን ለመቀነስ የሚችል አልነበረም። እሳቱ የተነሳው የወንዶች መኖሪያ ጋር በመሆኑ ታሳሪዎች ‹‹ከአደጋው ታደጉን›› የሚል ጥሪ አቀረቡ። በጀርባ እሳት አለ፤ በፊት ለፊት ደግሞ ጥይት ተደግኗል።

” የበአታ ማረሚያ ቤት ማኅበረሰብ ከ3000 ይበልጣል። ቀውጢ ሆነ፤ ጩኸቱ በዛ። ቅዳሜም ሆነ አራዳ ገበያ ከማረሚያ ቤቱ ሩቅ አይደለም። ኅብረተሰቡ ከእሳት አድኗቸው የሚል ጥያቄ አቀረበ። ብዙ ታራሚዎች አጥር እየዘለሉ ወደ ሕዝቡ ተቀላቀሉ። ከፊሎች ሲዘሉ መትረጊስ ቀደማቸው። ሰው በሰው ላይ አስከሬን በአስከሬን ላይ ተነባበረ። በሙታ በሙታን ላይ፣ሙታን በሕያዋን ላይ ወዳደቁ። ሰቆቃው ያኔ ነው የጀመረው። በሰዓቱ አንዲት ከአምስት ዓመት በታች የሆነች ሕጻን ይዛ እስረኛ ለመጠየቅ የገባች እናት ከፊቷ የሚወዳድቁ ሙታንን ስትመለከት ሕሊናዋን ሳተች፤ ልጅ መያዟንም ረሳች። በደመነፍስ ወደሚተኩሱት ወታሮች እየሮጠች እንዲያድኗቸው ተመጸነች። የሙታን ደም ባጨቀየው መሬት ላይ በሰደፍ ተመታ ወደቀች። ውስጥ ልጆቻቸው፤ ባሎቻቸውና ዘመዶቻቸው የታሰሩባቸው እናቶች ዋይታ በጽሑፍ የሚገለጽ አይደለም፤ እናቶች መቀነታቸውን አጥብቀው በሲቃ አስፓልት ላይ ሲንከባለሉ ማየት እንዴት ባለ ቋንቋ መግለጽ ይቻላል? ‹‹ወይኔ ልጄ! ወይኔ አባቴ! ወይኔ ወንድሜ! ወይኔ ጓዴ!›› የሚሉ ድምጾች ትናጋ እስኪሰነጠቅ ድረስ በዚያም በዚህም ይሰሙ ነበር። የተሰባሰበው ሕዝብ እስረኞች በእሳት እንዳያልቁ አጥብቆ ተመጸነ፤ አልሆነም፤ በየቦታው ሲንቀሳቀስ የነበረ ሰው ድፍት ይል ጀመር። ሕያው አካል በሰኮንድ ግዑዝ በድን ሲሆን ይታያል። ወጣቶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አቃታቸው። ድንጋይ መወራወር ተጀመረ። የፖሊስ ጥይት ዒላማው የሰው ልጅ ደረትና ጭንቅላት ሆነ። እስረኞች የሚሞቱት እየሞቱ በእሳት ከመበላት ጥይት ይሻላል በሚል ስሜት ከመትረጊስ ጥይት ጋር እሽቅድድም ጀመሩ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርኩት አንድ ወጣት ‹‹ምርጫው እኮ በእሳት ወይስ በጥይት መሞት የሚለው ነው፤ የትኛው ያሰቃያል?›› ሲል መልሶልኛል። ከእሳቱ ለማምለጥ የከመትረጊስ ጋር የሚታገሉ እስረኞች ቁጥር ሲጨምር ፖሊሶች መሣሪያቸውን ታጥቀው ከግለሰቦች ቤት ጣሪያ ላይ በውጣት አነጣጥረው መግደል ጀመሩ። የሚሞት አስከሬን ወደ ግቢው ነው የሚሸከፈው። አንዳንድ ፖሊሶች የሚሮጡ ታራሚዎችን ተከትለው በመሄድ እነርሱን ሲያጡ ያገኙትን ንጹህ ዜጋ ገድለው ይጎትቱም ነበር። አንድ ታራሚን ለመያዝ የሁለት ሕጻናት ጭንቅላት በጥይት ፈርሷል። አንድ ፖሊስ አንድ እስረኛን እየተከተለ ቅዳሜ ገበያ ላይ ሲደርስ ጠፋው፤ እዚያ አካባቢ ትንሽቱ መስጊድ አጠገብ ኳስ
የሚጫወቱ ሦስት ልጆችን አገኘ። ኳስ በእጁ የያዘውን ልጅ ግንባሩን አለው በጥይት። መቼም በዚህ ጊዜ ሕጻኑ እስረኛ መስሎኝ ነው አይባልም? አንድ አዛውንት ባጃጅ ውስጥ እንዳሉ የፌደራል ፖሊስ ዒላማ ሰላባ ሆነው ተዘረገፉ። ‹ፍቅር› እሚባል ካፌ ፎቅ ላይ ሻይ ሲጠጡ የነበረ ጎልማሳ ድፍት እንዳለ ነው የቀረው። የመኪናውን ጎማ ሲፈትሽ የነበረ ረዳት ቀበሌ 9 ከተጎነበሰበት ቀና ሳይል ቀረ። የሚሞቱ ሰዎች በሙሉ ወደ ማረሚያ ቤቱ ነበር አስከሬናቸው የሚወሰደው። ሕዝቡ ላይ ህጻን አዋቂ ሳይሉ ጥይትና የመርዝ ጋዝ በጅምላ አርከፈከፉ። የአቡን ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሰርቪስ አካባቢው ደርሰው ነበር። ሕጻናቱን የመርዝ ጋዝ ተረጭቶባው መኪና ውስጥ ሁሉም ወደቁ። ውኃ እየተደፋባቸው ነው መንቃት የቻሉት። የሕግ ታራሚዎች በምንም ይሁን በምን ከፖሊስ ፊት ከተገኙ መሞታቸው ቢያንስ ግን በጥይት እግራቸው መመታቱ ግዴታ ይመስል ነበር። ጻዲቁ ዮሐንስ አካባቢ በጭንቀት ያገኘዋት ልጅ በእንባ እየታጠበች ‹‹እኔ ሰው ሲሞት አይቼ አላውቅም። ጥይት እየጮኸ ሦስት ሰዎች በድንገት ደረሱ። አንደኛው ‹እባክሽ ፎጣ ስጭኝ› አለኝ። እኔም በድንጋጤ እምቢ አልኩት። ቀና ስል ሦስቱም ሕልም በሚመስል መልኩ ወድቀዋል። ሁለቱ እግራቸውን ነው የተመቱት፤ ፎጣ የጠየቀኝ ልጅ ግን ከአንገቱ ሥር ደም ሲወጣ ቀና ብሎ መልሶ ከንበል አለ›› በማለት በጭንቀት ውስጥ ሆና ነው የነገረችኝ። ሕዳር 21 ቀን ጎንደር ላይ ሞት ነግሦ ዋለ። የተጠራቀሙ አስከሬኖች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል – ቸቸላ – ተወሰዱ። በዚህ ቀን የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ ያለው ዳታ የተለያየ ነው። የሞቱ ሰዎች ከማረሚያ ቤቱ አምልጠዋል የተባለበት አጋጣሚ ሁሉ አለ። ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ አስከሬኖች 22 እንደሆኑ ነው ከተለያዩ ምንጮች ያረጋገጥኩት። ሆኖም በጊዜው በሰዓቱ አካባቢው የነበሩ ሰዎች ሳነጋገር ብዙዎቹ የሕግ ታራሚ ብቻ 38 ሰው ሞቷል ብለዋል። ከውጭ ያሉ ንጹሐን ሰዎችን ጨምሮ ሕዳር 21 ቀን የሞቱ ሰዎች ከ45 ይበልጣል ይላሉ ያነጋገርኳቸው ብዙ ሰዎች። ከፖሊስና ከከንቲቫ ጽሕፈት ቤት ለማረጋገጥ ያደረግኩት ሁሉ ስኬታማ አይደለም። ሆኖም አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የፖሊስ አባል በውል ማወቅ ቢከብድም ከ22 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ነው የተናገረው። ሆስፒታል ረቡዕ ዕለት ዝግ ቢሆንም ሐሙስ በጠዋት ግን ከገቡ በኋላ የሞቱ ሰዎችን ስም ዝርዝር ለጥፈው ነበር። የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ግን 16 ሰው ብቻ ተረጋግጦ ሞቷል ሲል እንደዘገበ ሰምቻለሁ። ይህ አይነት ሸፍጥ አዲስ አይደለም። አደባባይ ኢየሱስ ቤተ ከርስቲያን ውስጥ በ86 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ዋዜማ የተረፈረፉትን ንጹሐን ሰዎች በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከንቲቫ ጽሕፈት ቤቱን ሊዘርፉ የሞከሩ የቀድሞው ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል በማለት ከዘገበ ከ22 ዓመት በኋላ ኢሕአዴግ ያንኑ ውሸት ዛሬ ደገመው። ቀደም ባሉ ቀናት በብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ከወሰነላቸው ሦስት ጓደኛሞች መካከል አንደኛው ብር አጥቶ ሳይፈታ ይሰነብታል። የእርሱ የቅርብ ዘመድ የሆነ ችግሩ መፈጠሩን ሰምቶ ከመተማ አካባቢ መጣ። ስለመኖር አለመኖሩ እርግጠኛ አይደለም። ሆስፒታል አስከሬን ክፍል ከተደረደሩ አስከሬኖች መካከል ፈልግ መባሉን ሆኖም እንዳጠው ገልጧል። ረቡእ ጠዋት አንገረብ አጠገብ ወደ ተሰራው አዲስ ማረሚያ ቤት ታሳሪዎች ተዛውረው ነበር። ሐሙስ ጠዋት የታሰረ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አዲሱ ማረሚያ ቤት ምግብ ይዘው ወረዱ። ዋና ዓላማቸው ግን ምግብ መውሰድ አልነበረም፤ በሕዳር 21 ቀኑ ጭፍጨፋ መትረፍ አለመትረፋቸውን ለማረጋገጥ ነው እንጅ። ልዩ ኃይል ፖሊሶች መቅረብ አትችሉም ሲሉ ከለከሉ። ከውስጥ የሕግ ታራሚዎች ‹‹በረኀብ አለቅን›› የሚል ድምጽ ከብዙ ርቀት ይሰማ ነበር። በግምት ከረፋዱ 5፡00 ይሆን ነበር። እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ የፖሊስ አባላት በፒያሳ መስቀል አደባባይ አድርገው ወደ አዲሱ ማረሚያ ቤት ገሰገሱ። ሕዝቡን ለማስፈራራት ይመስላል። ከውጭ በጠያቂና በፖሊስ ከውስጥ በታራሚና በፖሊስ መካከል ግጭት ተከሰተ። ግቢ ውስጥ ያለው እሳር ተቃጠለ። ከውጭ በኩል የሄደው ጠያቂ መትረጊስ ሲጮኽበት በድንጋይ መመለስ እንደማይችል በመገንዘብ ተበተነ። ውስጥ ያሉት ግን ከመረሸን አላመለጡም።

“,እነሆ ሐሙስ ሕዳር 23 ቀን የተጨማሪ ሰዎች ደም ፈሰሰ። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሙታንንና ቁስለኞችን ተቀበለ። እንደተለመደው ሆስፒታሉ ተዘጋ። አንድ የልዩ ኃይል ፖሊሲ በዚህ ቀን የሞቱት 7 ናቸው ብሎኝ ነበር። ሆኖም ከሆስፒታል
ባገኘሁት መረጃ ግን የሟቾች ቁጥር 21 ነው። ከነዚህ ውስጥ 2ቱ ከገቡ በኋላ ነው ሕይወታቸው ያለፈው። ሐሙስ ለአርብ ሌሊት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የሰዎች መሪር ለቅሶ ነበር። ቀኑን የተገደሉ ሰዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ከተሰጠ በኋላ በመለዋ ጎንደር ለቅሶና ዋይታ ሆነ። ቀበሌ 18 ከአንደኛው ሟች ቤት ሄድኩ። ሐዘን ቤት ብዙ ቦታ ሂጄ አውቃለሁ። ለምን እንደው ባላውቅም ግን ከዚህ ቤት የነበረው ሐዘንና የቤተሰቦቹ ሐዘን ከእስካሁኑ የተለየ አደረገብኝ። ቲኬት አልነበረኝም፤
ግን ጎንደር በመቆየት ሐዘኑን መቋቋም አቅም አጣው። ለሁልጊዜው የማልሰለቻት ጎንደርን አርብ ጠዋት ትቻት ወጣሁ … ” ብሎ ያየ የሰማውን ጋዜጠኛው ሙለቀን ተስፉ ይነግረናል !

“ገኖ ባልተሰማው የጎንደሩ ወህኒ ቤት እሳት ቃጠሎና አደጋ ሀገሬው አዝናል ፣ ተቆጥቷል ! “…አምባገነን አስወገድኩ ፣ የሚል የኢህአዴግ መንግሰት አምባገነን ሆኖ ግፍ መፈጸሙን ማቆም አለበት! ” እያሉ የቁጣ ጭምር የሚናገሩት ቁጥር ቀላል አይደለም …ይህ መሰሉ ግፍ ምሬትን አርግዞ ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው የምንል ህዝቦች ወደ ሌላ የጦርነት አዙሪት ሊያስገባ ወደ ሚችል ፍጻሜ እንዳያመራ የሚመክሩም አልጠፉም ። አዎ! በአሁን ጌቶቻችን ባልታጠቀ ሰላማዊ ሰልፈኛ የጠመንጃ ምላጭ ስበው ህይዎት ሲቃትፉ ማየት አንሻም ! በህግ ከለላ በእስር ላይ ያሉ ዜጎች በሚኖሩበት ወህኒ እሳት ቃጠሎ ተነሳ ብሎ ከእሳት የሚሸሸውን ዜጋ በጠመንጃ አረር መቀበል የለየለት ግፍ ነው ! ብቻ እዚህም እዚያም የከፋ አስተዳደር በደልና ግፍ ሲፈጸም ማየት መስማት ሰልችቶናል … በጉልበት መታበይና ትውልድ ተሻጋሪ ግፍ መፈጸም በሰለጠነ ዘመን ማየት የሌለብን ሰይጣናዊ ባህሪ እንጅ የሰው ዘር ባህሪ ሊሆን አይገባም ፣ ግፍ ሊበቃ ይገባል !

የሞቱትን ነፍስ ይማር !

ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 28 ቀን 2008 ዓም

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.