የአማራ ስቃይ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ዉስጥ

የአማራ ስቃይ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ዉስጥ :- አመያ፤ አምሣለ ሰዶም ወገሞራ (የዘር ፖለቲካ ውጤት!) = (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ቅጽ 3፡ ቁጥር 22)


(የሰዶምና የገሞራ ሰዎች የጠፉት በሠሩት ሀጢያት ነው፡፡ ይህ አብረን የምናየው ቀየ የጠፋው ግን ያለምንም ወንጀል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እኔ የሶዶምና የገሞራ ምሳሌ ያልኩት በእሳት የመጥፋታቸውን መመሳሰል ብቻ መሆኑን አንባቢ እንዲረዳ አስገነዝባለሁ)፡፡

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ የታሕሳስ መባቻ ጀምሮ በጎሳ ግጭት ምክንያት እየተፈጠረ ስላለው ውድመት ከቦታው የሰቆቃ መልእክቶች ደረሱኝ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ‹‹የእንታደጋቸው ጥሪ›› ሳስተላልፍ ብዙ ሰዎች ሊያምኑኝ አልፈለጉም፤ ወይም የባላገሮቹ ሰቆቃ ወጥቶ እንዲሰማ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ምክንያቶቹን ለመዘርዘር አልሻም፡፡ ለራሴ ግን ሂጄ ማስረጃዎችን ይዤ መመለስ እንዳለብኝ ቃል ገባሁ፤ አደረግኩትም፡፡

ታሕሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ ለመሄድ ከአውቶቡስ ተራ ተሳፈርኩ፡፡ ወሊሦ ከተማ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን አንዲት የመከላከያ መኪና የእቃ መጫኛ ላይ አንድ ግሉኮስ የተተከለለት ወታደር በሌሎች ሁለት ጓዶቹ ተደግፎ አየነው፡፡ የነበረው ግጭት እጅግ ከባድ እንደነበር ለመገመት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ወሊሶ ከተማ ስንገባ የከተማ አስተዳደሩ ግቢ የመከላከያ ሚንስትር ይመስል ነበር፡፡ ስንት ጋንታ ጦር ወሊሦ እንደተመደበ መገመትም ማወቅም አይቻልም፡፡ አካባቢው ሁሉ አረንጓዴ ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች ብቻ ነው፡፡

ከቱሉ ቦሎ ጀምሮ በየመንገዱ ዳር ያሉ ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች አንድም ፈራርሰዋል፤ አሊያም ተቃጥለዋል፡፡ የፖሊስ ጣቢያ የነበሩ ቢሮዎች ሁሉ ተደረማምሰዋል፡፡ በአስፓልት ዳርና ዳር በሜትር ኩብ ሊሸጡ የሚችሉ ድንጋዮች ተደርድረዋል፤ ገዥ ስምምነቱን አፍረሶ በታትኖት የሄደ ነው የሚመስለው፡፡ ከአንድ ቀን በፊት አስፓልት ላይ ተከምረው የነበሩ ‹አማጺ› ድንጋዮች ነበሩ፡፡ ወልቂጤ መናሐሪያ ወረድኩ፡፡ በየቦታው መድረሻ ያጡ ተፈናቃዮችን አየሁ፤ እያንዳንዳቸውን የተወሰኑ ሰዎችን ሳናገር ከዚህ ሙሉውን ቀን ባሳልፍም ችግራቸውን ሰምቼ እንደማልጨርሰው በመገንዘብ ትቻቸው ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ከወልቂጤ 42 ኪሎ ሜትር ወደምትርቀው ዳርጌ ከተማ ሄድኩ፡፡ ዳርጌ ከተማ ስደርስ ከቀኑ 6፡00 ሆኖ ነበር፡፡

የዳርጌ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ድንበር ላይ የምትገኝ የጉራጌ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ በሚያዚያ 2007 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የኖኖ ወረዳ የኦህዴድ ባለስልጣናት አስተባባሪነት ሙሉ ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው አማሮች ከዚህች ከተማ በቀን ሥራም ባተሌም ሆነው አሉ፡፡ ጥሬ ገንዘብ ብቻ 492 ሽህ ብር የተቃጠለበት አንድ ገበሬ ‹‹እንሻገርና ቤት ሰርተንላቸዋለን እያሉ የሚያወሩትን ላሳይህ›› አለኝ፡፡ ሞተር ተከራዬንና ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመግባት ተነሳን፡፡ ተጎጅው ሰው አውራሪስ ይባላል፡፡ አውራሪስ ለሞተረኛው ማስጠንቀቂያ ሰጠው፡፡ ‹‹ማንም ሰው ወደ እኛ ከመጣ ይዘህን መሮጥ አለብህ፤ ለማንም በምንም መልኩ መቆም የለብህም›› አለው፡፡ አውራሪስ ያሰበው ለእርሱ ደህንነት አልነበረም፡፡ እኔ እነርሱ ጋር ሂጄ አንዳች ችግር እንዳይገጥመኝ በመሥጋት እንጅ፡፡ የብሔር ፖለቲካችን አሳፋሪነት ከምንግዜውም በላይ የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከዳርጌ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር እንኳ አልራቅንም፡፡ ግን ሞተረኛው ወደ ጉራጌ ዞን (ዳርጌ ከተማ) ይዞኝ ድልድዩን ከተሻገረ ምንም እንደማልሆን እሙን ነበር፡፡ ምንም እንኳ በየትኛውም ቦታ ሂጄ መረጃ የመሰብሰብ ነጻነት ቢኖረኝም ጥንቃቄ ማድረጉን አልጠላሁትም፡፡

ባለፈው ዓመት የተቃጠለው ቤት አመድ ትንሽ ትንሽ ኮረብታ በየቦታው ሰርቷል፡፡ እንኳን ለሰው ለእንስሳ የማይሆኑ አሊያም አልፎ ሂያጅን ሰው ዝናብ እንኳን ማስጠለል የማይችሉ ቤቶች ከአራት ማዕዘን ከቆሙ ትንሽ እንጨቶች ላይ ከ5-10 ዚንጎ የሚሆኑ ቆርቆሮዎች በሚስማር ተያይዘዋል፡፡ የአካባቢው መንግሥት ለተጎዱ ወገኖች ቤት ሰርተንላቸዋል ያለው እንደሆነ ገባኝ፡፡ ሆኖም እንዳልኩት እንኳን ሰው እንስሳም አልተጠለለባቸውም፡፡ አካባቢው እስካሁን ምድረ በዳ ነው፡፡ ፎቶ ግራፎችን ካነሳሁ በኋላ ሞተረኛችን ይዞን እንዲሮጥ መመሪያ ከአውራሪስ ተሰጠው፡፡ ሾፎሩን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ያዘለችው ሞተር ሸመጠጠች፡፡ ከፊት ለፊታችን ሁለት ሆነው ወደእኛ አቅጣጫ የሚሮጡ ሞተረኞች አየን፡፡ በቅጽበት አቅጣጫ ስተው ሞተሯ ወደ ሰማይ ተነስታ ሁለቱም ጋላቢዎች የተለያየ አቅጣጫ ወደቁ፡፡ ነገሩ ሁሉ ፊልም ነበር የሚመስለው፡፡ አንደኛው ወዳቂ በደመነፍስ ተንሰቶ ወደ እኛ አየ፡፡ ሰከንድ አልቆየም፤ ተመልሶ ወደቀ፡፡ ሰው ተሰበሰበ፡፡ ግን አልቀረብንም፡፡ እንዴት እንደሆኑም ወሬ አልሰበሰብኩም፡፡ ቶሎ ወደ ጉራጌ ዞን ገባን፡፡

ከሌላኛው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ክፍል አመያ ወረዳ ተፈናቅለው ከመጡ ሰዎች አንዱን ወጣት ይዘን ወደ ሰሞነኛው የጥፋት ቦታ ለመሄድ ተነሳን፡፡ አውራሪስም አብሮን ይሄድ ስለነበር ሌላ ሞተር አስፈለገን፡፡ አውራሪስና አብሮን እንዲሄድ የተነጋገርነው ወጣት በአንድ ሞተር እኔ ብቻዬን በሌላ ሞተር ሆነን ጉዞ ጀምረን፡፡ ወደ ወልቂጤ መንገድ 15 ኪሎ ሜትር ያክል እንደተጓዝን ዋልጋ የምትባል ትንሽ ከተማ አለች፡፡ ይህች ትንሽ የፍየል ግንባር የማታክል መንደር ከአቅሟ በላይ በባላገሮች ተጥለቅልቃለች፡፡ ብሶተኛ በሞላበት አገር ብሶትን የሚያዳምጥ ሰው ውድ ይሆናል፡፡ ሞተር አቁመን አንዱን ነጠል አድርጌ ስለሁኔታው ስጠይቀው ብዙዎች መጥተው ከበቡን፡፡ ሁሉንም ለመስማት እንኳንስ በዚያች አጭር ሰዓት ቀርቶ ወራትንም እንደማልጨርሰው ስገነዘብ ባድማቸውን አይቼ ለመምጣት ተሰናብቼ ሞተሬ ላይ ተፈናጠጥኩ፡፡ ከዋልጋ ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ታጥፈን 2 ኪሎ ሜትር እንኳ ሳንጓዝ እኔ የምጋልባት ሞተር ጎማ ተነፈሰ፡፡ ምርጫ አልነበረኝም፡፡ የእነ አውራሪስ ሞተር ሾፌሩን ጨምሮ አራተኛ ሰው ሆኜ ተፈናጠጥኩ፡፡ ባልተስተካከል አባጣ ጎርባጣ የገጠር መንገድ አንዲት ሞተር ላይ አራት ሰው መንጠላጠል ምን ያክል ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ቀላል አይሆንም፡፡ በሕሊናዬ የማስበው ቀደም ሲል ኖኖ ወደ ሰማይ ነጥረው የወደቁትን ጋላቢዎች ነው፡፡

ሆኖም ከዋልጋ ተነስተን ሁዳድ ሁለት እስከንደርስ ድረስ በየመንገዱ የማያቸው የሚያሙ ደረቅ እውነቶች ሁሉንም ነገር አስረሱኝ፡፡ ከዋልጋ እስከ ሁዳድ ሁለት ያለው እርቀት 12 ኪሎ ሜትር ያክል ነው፡፡ በዚህ ሁሉ እርቀት ብዙ አይነት ትእይንት አለ፡፡ በአንዱ እያዘንኩ በሌላው እየተከዝኩ ጉዟችን ቀጠልን፡፡ እንደተቃጠለው ቤታቸው ሰውነታቸው ላይ ጥቅርሻ የተሸከሙ፣ ቆብ ደብፍተው ከጉዞ ብዛት ደክሟቸው መንገድ ላይ ተኝተው ይሁን ወድቀው እንደሆነ ለማወቅ የሚከብድ አሮጊቶች፣ በጀርበዋ በአንቀልባ አዝላ በፊቷ አሞንቅላ በኋላዋ ሌላ ጉብል የምታስከትል እናት፣ ልጁን አሽኮኮ ብሎ ውሻውን በገመድ የሚጎትት አባት፣ በአህያ ጋሪ ቅራቅንቦ ጭነው ወደ ፊትም ወደ ኋላም የሚጓዙ መንገደኞች፣ በጉራጌዎች መንደር ድንኳን ውስጥ የሚርመሰመሱ ነፍሳት፣ ዛፍ ጥላ ስር በሕብረት የተቀመጡ ሰዎች፣ ወደ ፊትም ወደ ኋላም እንዳይንቀሳቀሱ በቡድን የሚጠበቁ ከብቶች… ይህ ሁሉ ትእይንት በዚህ ቦታ አለ፡፡ መንገዱ ሁሉ በርበሬ እንደ ዓመት በዓል ቄጠማ ተጎዝጉዞበታል፡፡ ሰው በርበሬ ያልተደፋበት መንገድ ላይ አልሔድም ብሎ ያስቸገረ ይመስላል፡፡ ምንም አይነት ሰው በአካባቢው ባይኖር እንዴት እኔ በአልጫ እየበላሁ እዚህ መሬቱ ሁሉ በርበሬ በበርበሬ ይሆናል? ብየ እቆጭ ነበር፡፡

በደርግ በሰፈራ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች የሚኖሩባቸው ሰፈሮች ሁዳድ ይባላሉ፡፡ በአበሽጌ ወረዳ (ጉራጌ ዞን)ና በአመያ ወረዳ (ደቡብ ምእራብ ሸዋ) አስር የሁዳድ ሰፈሮች አሉ፡፡ 10፡00 አካባቢ ሁዳድ ሁለት ደረስን፡፡ መከላከያ ሰራዊት አስቆመን፡፡ የሁዳድ ሁለት ጤና ጣቢያ የጦር ካምፕ ሆኗል፡፡ ሁዳድ ሁለት የምትባለው ትንሸ ከተማ ናት፡፡ ሆኖም በጊዜው መንገድ ለመንገድ መሄጃ ጠፍቷቸው ብኩን ከሆኑት የአማራ ገበሬዎች ውጭ አንድም እንኳ ሰው አልነበረም፡፡ ቤቶች ሁሉ ተቆልፈው ሰው አልባ ናቸው፡፡ ከቃጠሎ ለማምለጥ ርቀው እንደተሰደዱ ሰማን፡፡ የመከላከያ ኃላፊውን ሰው አናገርኩት፡፡ በዚህ ሰዓት መግባት አትችልም አለኝ፡፡ ለመንኩት፡፡ ወታደሩም ገብተህ አንድ ችግር ቢገጥምህ ኃላፊነቱን አልወስድም ሲል ሞገተኝ፡፡ እንዲያጅቡኝ ብጠይቃቸውም ፈቃደኞች አልሆኑልኝም፡፡ ሆኖም ጋዜጠኛ እንደሆንኩ ያወቁ ተሰደደው የነበሩና መረጋጋቱን ለማረጋገጥ የመጡ የሁዳድ ሁለት ነዋሪዎች ‹‹እኛ ይዘነው እንገባለን›› አሉ፡፡ መከላከያዎች ፈቀዱልን፡፡ አውራሪስን፣ ከዋልጋ ይዤው የመጣሁትን ወጣትና የሞተሯን ሾፌር እዚያው እንዲጠብቁን ነገርን እዚያ ያገኘዋቸውን ሁለት አዲስ ወጣቶች ይዤ ገባሁ፡፡ መንገድ እንደጀመርን ሞተሯን የሚነዳው ልጅ ‹‹መከላከያ መሣሪያ አልያዝንም እኮ›› አለ፡፡ ጠመንጃ ሳንይዝ ስለገባን ሕልውናችንን ለእግዜር አደራ ሰጥተን ወደ ፊት ገሰገስን (በነገራችን ላይ በዚያ አካባቢ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤት ባይኖርም ሁሉም ሰው ሞተር መንዳት እንደሚችል አረጋግጫለሁ)፡፡

አሁን በገባሁበት አገር የምንተነፍሰው አየር ቃጠሎ ቃጠሎ የሚል ነው፤ የጢስ ዶዱራንት በአገሩ ሁሉ የተረጨ ነው የሚመስለው፡፡ አቧራውም አመድ ነው፡፡ ዝር የሚል የሰው ዘር የለበትም፡፡ ከሁዳድ ሁለት ጀምሮ ወደ ፊት በግምት 20 ኪሎ ሜትር ያክል ብንሄድም ከቤተ ክርስቲያን ወይንም ከመስጊድ ውጭ ቆሞ የሚታይ ቤት የለም፡፡ ሦስት የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በዚህ አገር ተረት ሆነዋል፤ ቤቶች አምደዋል፡፡ የቤት አሰራራቸውን ለማጥናት የሚፈልግ ባለሙያ እንኳ ቢሄድ ለናሙና (ሳምፕል) ሆኖ የሚያገለግል አንድም እንኳ ቤት ፈልጎ ማገኘት አይችልም፡፡ እዚህ አገር እነማን ነበሩ ብሎ የሚጠይቅ ሰውም አቅጣጫ የሚሳይ ግለሰብ ከየትም አይገኝም፡፡ ነዋሪዎች በሙሉ ቤታቸውን አንድደው ሞቀው ተመካክረው የጠፉ ነው የሚመስለው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃቸው የሶዶምና የገሞራ ሰፈሮች ላይ የዘነበው የእሳት ዲን በዚህ አገር ላይ በዚህ ዘመን የሆነ ነው የመሰለኝ፡፡ ኦ አመያ! አምሣለ ሶዶም ወገሞራ! የሶዶምና የገሞራ ምሳሌ በሆነችው የአመያ ወረዳ ያሉ ሦስት ቀበሌዎች (ቢሊ (በሬዳ)፣ ቀርሳ ቁሊት (ኩኖ ቁሊት)ና ጎንበሬ የቀበሌ ገበሬ ማህበራት) ቤት ሙሉ በሙሉ አምደዋል፡፡ በጎተራዎች የነበሩ እህሎች በሙሉ የሰው ሆድ ሳይሆን የእቶን ላንቃ በልቷቸዋል፡፡ የቤቱን ግድግዳና ጣሪያ የጨረሰው እሳት እህሉ እስካሁን አቆይቶት ሲጨስ አልፎ አልፎ ይታያል፡፡ ቀዩ በርበሬ ነጭ አመድ ሆኗል፡፡ ቦሎቄው አንድም አምዶ አሊያም ቆሎ ሆኖ አለ፡፡ ታዲያ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው ቤት ስንሄድ የምናገኛቸው ውሾችን ነው፡፡ ባለቤተቹ ከተሰደዱ ቀናት ቢቆጠሩም ውሾቹ በታማኝነት አመዱ ላይ ተኝተው የጌቶቻቸውን መመለስ በርሃብ እየተገረፉ ሲጠብቁ ስመለከት ምን ያስቡ ይሆን አልኩ ለራሴ፡፡

ከአንድ አስር ያክል ቤቶች ከተቃጠሉበት ግቢ ያየኋት ውሻ ግን አስለቀሰችኝ፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ እንባ አይወጣኝም፤ ደረቅ ሰው ነበርኩ፡፡ ከዚህ የአመደ ባድማ ያገኘዋት ውሻ ከሳምንት በላይ የጌቶቿ የተቃጠለ ቤት ላይ ተኝታ በምግብና ውኃ እጦት ከተኛችበት መነሳት አቅቷታል፡፡ ስታዬን ተኝታ ጅራቷን ቆላች፡፡ ቀረብኳት መነሳት አትችልም፡፡ ለምን እንደሆነ አላወቅኩም የእንባዬ ከረጢት ተፈታ፡፡ በሕይወቴ ብዙ አስቀያሚ ነገሮችን አይቻለሁ፡፡ በደርግና በህወሓት መካከል በተካሄደ ጦርነት እናቴ ጀርባ ላይ ታዝዬ ስንሰደድ ከፊታችን ሰውም እንስሳም እየተመታ ሲወድቅ በህጻን አእምሮየ ተቀርጾ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ በየሜዳውና ጫካው ቀባሪ ያልነበረው ሬሳ ሁሉ ወዳድቆ የአሞራ ቀለብ ሲሆን አይቻለሁ፡፡ በብስለት ዘመኔ ካየሁት ግን ይህን ያክል የሚያሰቅቅ ነገር የለም፡፡

ከአንዱ ወደሌላኛው አካባቢ ብንሄድም አንድም እንኳ የቆመ ቤት አላገኘንም፡፡ ዋሾ ላለመባል አንድ ቦታ ላይ ብቻ የቤቱ ግማሽ ጎኑ ተቃጥሎ በአንድ በኩል ያለው ግድግዳ ቀርቶ የዘመመ ቤት አይቻለሁ፡፡ የመቃብር ቤቶች ተቃጥለው የቤተ ክርስቲያኑ በረንዳም ተቃጥሎ አይቻለሁ፡፡ መንገድ ለመንገድ የተዘራ በርበሬ ሞልቷል፡፡ የተደፋ ቦሎቄም እንዲሁ፡፡ ቦሎቄ በጄ ዘግኜ ቦርሳዬ ውስጥ ጨመርኩ፡፡

አብረውኝ የነበሩ የሁዳድ ሁለት ልጆች እኔ ሳነባ እነሱ አጽናኑኝ፡፡ አማራ የሚባል የፋሲካ በግ ምን አገር አለው አሉኝ፡፡ አገራችሁ የት ነው ልበላቸው? እነዚህ ወጣቶች እንደነገሩን አንድ ቤት ውስጥ የሞተ አስከሬንም አብሮ ተቃጥሏል፡፡ አጓጉል እድሜ ላይ ያሉ የጠፉ ሕጻናት የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ ይቃጠሉ አይቃጠሉም ማንም አያውቅም፡፡ የምር ግን እዚህ እንደጻፍኩት ቀላል አይደለም፡፡ ምንም አይነት አማርኛ ብጠቀም እዚያ ያለውን ትእይንት መግለጽ አልችልም፡፡ ከአመድ አመድ ሰይጣን ይመስል ስንዞር ቀኑ መሸብን፡፡ ወጣቶቹ ከዚህ በኋላ ለሕይወት አስጊ ነው እንውጣ ባይሉኝ ኖሮ መሄድ እንዳለብኝም ሳልረሳው አልቀረሁም፡፡ በአገሬ ላይ ምንም ተስፋ አጣሁ፡፡ ሞተሯ ተነሳች፡፡ እኔ መካከል ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ወደ ሁዳድ ሁለት ተመለስን፡፡ በአንድ እጃቸው ገጀራ የጨበጡ ጢስ ጢስ የሚሸቱ ብዙ ሰዎች ከበቡኝ፡፡ አንዳች የተስፋ ቃል የምነግራቸው አልነበረኝም፡፡

ፊታቸው ላይ እልህ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ባይተዋርነት፣ በቀል፣ … እነዚህ ሁሉ በአንድነት በፊታቸው ላይ ይነበቡ ነበር፡፡ ቤታቸው የተቃጠለበትን ምክንያት ጠየቅኳቸው፡፡ ወንጀሉ ‹‹አማራ መሆናችን ብቻ ነው!›› አሉኝ ሁሉም በአንድነት፡፡ በእያንዳንዱ ቤት በአማካይ የተቃጠለው የበርበሬ ምርት ብቻ ከ70 ሽህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

እነማን ቤታቸውን እንዳቃጠሉባቸው ስጠይቃቸው ‹‹የኦነግም የኦዴድም መታወቂያ ያላቸው ሰዎች ተይዘዋል፤ ሕብረተሰቡን ያስተባብሩታል እየሸለለ በሕበረት መጥቶ ያቃጥለናል›› አሉኝ፡፡ ቀደም ሲል ኖኖ ወረዳ ላይ ያሉ አማሮች ቤታቸው እንዲቃጠል ያደረጉ የፖሊስ አባላትም እንደተሳተፉበት ነግረውኛል፡፡ አማሮችም በአጸፋ የትንሽ ኦሮሞ ገበሬዎችን ቤቶች እንዳቃጠሉ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ፀሀይ ወደ መጥለቂያዋ እየሮጠች ነው፡፡ መመለስ አለብኝ፡፡ ሁሉንም ሰው የምሰማበትም ጀሮ የለኝም፡፡ ስሜቴ በአየሁት ነገር ደንዝዟል፡፡ ለእነዚህ አማሮች ሎጥ ከቃጠሎ የተዳነበትን ዙአር ተራራ ማሳዬት አልችልም፡፡ እንኳን እነርሱን ላድን ለእኔም የማልሆን ለፍስፍስ ነኝ፡፡ አቅመ ቢስነት እንደዛሬ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡

በጉራጌዎች ድንኳን የተሰበሰቡ ሰዎችን አልፎ አልፎ ሳናግር ያስጠለሏቸው ሰዎች ሸክም ሳይከብዳቸው እኔም ቡና እንድጠጣ ይጋብዙኛል፡፡ የተከራየናት ሞተር ባለቤቱ የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ግን ችግር ቢከሰት ይዞን እንደሚሮጥ እነ አውራሪስ ሙሉ እምነት ጥለውበታል፡፡ ዝብርቅርቅ ያለ ነገር ተሰማኝ፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ ይህን ያክል መተማመን አለ፡፡ ታዲያ ምን ጎደለን? ታዲያ በሕብረት የአማሮችን አገር እንደሶዶምና ገሞራ ለምን በእሳት ይጠፋል? መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ! ኃይለኛ ራስ ምታት ያዘኝ፡፡ ወልቂጤ ከተማ ስገባ ምሽት አንድ ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ወሊሦ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 350 ያክል አማሮች እንዳሉ ነገረውኛል፡፡ አንድም መሽቶብኝ ሁለትም ምንም ላላደርግ ብዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ ሰውነቴ መድከሙን ያወቅኩት ምሽት አራት ሰዓት አዲስ አበባ ስደርስ ነበር፡፡ ከጦር ኃይሎች ወደ ሜክሲኮ ታክሲ ለመያዝ ስራመድ እግሮቼን ያዘዝኳቸው በግድ ነበር፡፡

ሙሉቀን ተስፋው

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.