ግለሰብ ፣ ተቋም እና ስርኣት በአመቻማች ባህል ዉስጥ ያላቸዉን ቀለበታማ ትስሰር መፍቻ ቁልፍን አሰሳ?

ግለሰብ ፣ ተቋም እና ስርኣት በአመቻማች ባህል ዉስጥ ያላቸዉን ቀለበታማ ትስሰር መፍቻ ቁልፍን አሰሳ?

ሸንቁጥ አየለ

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ለማብራራት እንደተሞከረዉ አመቻማች ባህል የዲሞክራሲ እሴትን ለመሸከም አቅምም ሆነ ፍላጎት የለዉም። በዋናነትም ይህ ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ በክፍል አንድ ለማዬት ተሞክሯል።

አንዳንድ የማህበረሰብ ጥናትና የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚያስቡት በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ የግለሰቦች ስነባህሪ የማህበረሱን ተቋማትና ስርኣት ሊቀርጸዉና ሊያንጸዉ ስለሚችል በማህበረሰቡ ዉስጥ የተጠናከረ ተቋማትና ስርኣት ቢኖርም ባይኖርም የግለሰቦች አስተዋጽኦና ስነባህሪ ማህበረሰብን ወደ ልዕለሀያልነት ሊመራዉ ይችላል ሲሉ ይተነትናሉ። ምክንያቱም ይላሉ ስርዓትም ሆነ ተቋማት ግኡዛን ሲሆኑ ዋናዉ ሞተር ግለሰብ ነዉና ግለሰቦች ግዑዛኑን ነገሮች ወደተሻለ ደረጃ በፈለጉት ሁኔታ ሊመሩዋቸዉም ሆነ ሊቀርጹዋቸዉ ምንም የሚሳናቸዉና የሚያቆማቸዉ ነገር የለም። ስለሆነም በጽንሰሀሳብ ደረጃ ስለስርኣትና ተቋማት ብናወራም በተግባር ግን ያሉት ግለሰቦች ናቸዉ ሲሉ የግለሰብን ዋና ሞተርነትና የአንድ ማህበረሰብ የልዕለሀያልነት መሰረትነትን ያብራራሉ። ስለሆነም ዋናዉ የልዕልና ሚስጥር በግለሰቦች ዙሪያ ማጠንጠን እንዳለበት ይመክራሉ።

ሌሎች ደግሞ ማህበረሰብ ከሁሉ በቀደመ ሁኔታ የተጠናከረ ስርኣትና ተቋማት ካሉት ብቻ በትክክለኛዉ መንገድ የግለሰቦችንም ሆነ የጠቅላላዉ ማህበረሰብን ባህሪ ፣ ፍላጎትና እራዕይ በመቅረጽና በአንድ የእሴትና የህግ ጠገግ በማስተሳሰር ወደ ታላቅ ብልጽግና ይመራል እንጅ የግለሰቦች ባህሪ/ቅድመ ሁኔታነት/ ቀዳሚ ሚናዉ ዝቅ ያለ ነዉ ሲሉ ይሞግታሉ።

የሁለቱንም ወገኖቾ አስተሳሰብ ወስደን እንኳን በአመቻማች ባህል መሰረት ላይ ብናቆማቸዉ አመቻማች ባህል ሁለቱንም አስተሳሰቦች ተሸክሞ የማቆም አቅሙ አጠያያቂ ሆኖ እናገኘዋለን።

ካለይ እንዳልንዉም አመቻማች ባህል ሀያላን፣ ባለአዕምሮ፣ የለዉጥ እና የፈጠራ አቅም ያላቸዉን ግለሰቦች አፍርቶ፣ ተንከባክቦና አጀግኖ ከማዉጣት ይልቅ ቢቻል ጨርሶ እንዳይወጡ አጨናግፎ፣ ከወጡም አኮስምኖ ምናልባትም አልኮሰምንም ብሎም አልጨነግፍም ያሉትን ወይ ገሎ ወይም ከሀገር አሳዶ ህይዎት አልቦ ጉዞ ስለሚጓዝ በመጀመሪያ ቡድን ዉስጥ ያሉ ሳይንቲስቶችን አስተሳሰብ ወስደን በአመቻማች ባህል ማዕቀፍ ዉስጥ ስንፈትነዉ ተንጦ የሚወጣዉ ቅቤ ስራስር የበዛበት ቅቤ አይነት ነገር እንጅ እዉነተኛዉ ቅቤ ሆኖ አይገኝም። ምክንያቱም ሀያላን፣ ባለአዕምሮ፣ የለዉጥ እና የፈጠራ አቅም ያላቸዉን ግለሰቦች በእርግጥም በማንኛዉም የስርኣትና የተቋማት መሰረት ላይ ቢቆሙና ያን ስርኣትና ተቋማት የሚመሩት ከሆነ ወደ ትክክለኛ አቅጫ ሊወስዱት እንደሚችሉ አያጠራጥርም። ሆኖም እንደዚህ አይነት ሀያላን፣ ባለአዕምሮ፣ የለዉጥ እና የፈጠራ አቅም ያላቸዉ ግለሰቦች ቀድሞዉንም በአመቻማች ባህል ዉስጥ በብዛት ማግኘት እጅግ ከፍ ያለ ፈተና ነዉ።

 

በሁለተኛዉ ቡድን ዉስጥ ያሉ ሳይንቲስቶች የሚያነሱትን የአስተሳሰብ መህልቅ አንስተን ስርአትና ተቋማት ቅድመ ሁኔታ ናቸዉ ብለን ስንፈትሽ ደግሞ የምናገኘዉ ዉጤት ከበፊቱ የባሰ አስፈሪ ነዉ። በአመቻማች ባህል ዉስጥ የሚቀረጹ ስርኣትና ተቋማት ትዉልድ የማይሻገሩ፣ በስሜት የሚቀመሩ እና የማህበረሰቡን አጠቃላይ ማንነት ተሸክመዉ /አቻችለዉ/ ማህበረሰቡም ሆነ ግለሰቦች ለፈጠራ፣ለነጻ አስተሳሰብና ለታላላቅ ሰበአዊ ስራ የማያነሳሱ በተቃራኒዊ ግን በግለኝነት የተተበተቡ አላዋቂነትን እና አድር ባይነትን የሚያበረታቱ ሆነዉ እናገኛቻዋለን። በአጠቃላይ በዚህ አይነቱ የባህል መሰረት ላይ የሚመሰረቱ ተቋማትና የሚዘረጉ ስርአቶች የማህበረሰቡን ስሜት፣ አመለካከት፣ እዉቀት እና ራዕይ በአንድ ገመድ አስተሳስረዉና በህግና በዘላቂ እሴት አዋቅረዉ ለአሁኑም ሆነ ለመጭዉ ትዉልድ በታማኝነት፣በዘላቂነት እንዲሁም ሁሉንም ሊያስማማና ለሁሉም የሚበጅ ሁኔታን የመፍጠር አቅማቸዉ ከዜሮ በታች ነዉ።

 

ከላይ እንዳዬንዉ ግለሰብ ፣ ተቋም እና ስርኣት በአመቻማች ባህል ዉስጥ ቀለበታማ ትስስራቸዉ በቀላል የሚፈለቀቅ ሆኖ አይገኝምና በእርግጠኝነት አንዱ የአንዱ ፈዉስ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ቀላል ሆኖ አይታይም። ስለዚህም አመቻማች ባህል ዉስጥ ተዘፍቆ የሚገኝን ማህበረሰብ ከተነከረበት አረንቋ መንጭቆ ሊያወጣዉ የሚችል ምን አይነት መፍትሄ ነዉ? የሚል ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም። ተገቢም ነዉ። ለዚህ ጥያቄ መልስ ፍለጋ የሚመለከተዉ ወገን ሁሉ በጥልቀት ማሰብ ያስፈልገዋል።

 

ምናልባት አንዳንድ ወገኖች እንዲህ አይነት ማህበረሰብን ከዚህ አረንቋ መንጭቆ የሚያወጣዉ የባህል አቢዮት ነዉ የሚል ታሳቢን በአዕምሮአቸዉ ማንሳታቸዉ አይቀርም። ሆኖም ስንዝር ሳይራመዱ የሚገጥማቸዉ ፈተና ለምሆኑ ይሄን የባህል አቢዮት የሚመራዉስ ማን ነዉ? የሚለዉን ጥያቄ ያነሱ እለት ነዉ። ምክንያቱም ከላይ እንዳነሳንዉ አመቻማች ባህል ዉስጥ የተዘፈቀ ማህበረሰብ ባለአዕምሮዎችን፣ ታማኞችን፣ ለእዉነት ከፍያለ ዋጋ የሚሰጡ የማህበረሰቡ አባላትን፣ ሰበኣዊነታቸዉ ከፍ ያሉ ግለሰቦችን፣ ግለሰባዊ የራዕይ ከፍታቸዉ እጅግ ከፍ ያሉ ምሁራኖችን ፈጽሞ የሚያስተናግድበት ቦታም ሆነ አቅም የለዉምና እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ማህበረሰባችን የባህል አቢዮት ያስፈልገዋል ብለዉ ወደ መድረክ የመምጣት እድላቸዉ እጅግ ዝቅተኛ ነዉ። ስለሆነም ባለአዕምሮዎች ያልመሩት የባህል አቢዮት ደግሞ ያለ እዉቀት እንደሚዉዘገዘግ ጎጅና ፈንጅ ሀይል እራሱን ማህበረሰቡን ሳይታሰብ ዞሮ ሊያጠፋዉ ስለሚችል ይሄኛዉስ አማራጭ ብዙ የሚያላዉስ ይሆን የሚል ተጠይቅን በአእምሮአችን ማጫሩ አይቀርም።

እናም ግለሰብ ፣ ተቋም እና ስርኣት በአመቻማች ባህል ዉስጥ እንዲህ ተቆላልፈዉና ተሰባጥረዉ አንዱ አንዱን አንቆ በአሉታዊ ኩነት አጠቃላይ የማህበረሰቡን እርምጃ የሚገታ ከሆነ ይሄን ቀለበታማ ትስሰር መፍቻ ቁልፍን የት ነዉ ማሰስ ያለብን ? የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ አዕምሮአችን ዉስጥ ማንቃጨሉ የማይቀር ነዉ።

የማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች የተመሰረቱት፣የቆሙት አንዲሁም የግንባታ ሂደታቸዉ በማያቋርጥ መልኩ በሁሉም ዘርፍ የተሳሰረዉ በጋራ ኤሴት / common values/ ላይ መሆኑን የሚተነትኑ የማህበረሰብ ምሁራን ደግሞ ከቅርብ አመታት ብኋላ በየዘርፉ በብዛት እይታቸዉን ማስነበብ ችለዋል። በእነዚህ ምሁራን ትንታኔ መሰረትም አንድ ማህበረሰብ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዉ አስከ ማህበራዊ መስተጋብሩ እንዲሁም ፖለቲካዊ ክወናዉ ድረስ የሚተሳሰርባቸዉ ብሎም ለታላቅነት ወይም ለኮስማና ማህበረሰብነት የሚያበቁት በመሃከሉ የገነባቸዉ የጋራ ኤሴቶች / common values/ ናቸዉ ሲሉ አጥብቀዉና አጥልቀዉ ያብራራሉ።

ይህ የጋራ ኤሴትን / common values/ በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ ፈልፍሎና ጎርጉሮ የማዉጣትና አዎንታዊ በሆነዉ እሴት ላይ በአስተዉሎት አዳብሮ በዚሁ አዎንዊ የጋራ አሴት መዳበርም ማህበረሰቡን የወረረዉን አመቻማችነት መፈወስ ይቻላል ወይ ? የሚለዉ ጉዳይ ቀልብ የሚስብ ሆኖ ይገኛል።

እንደሚታወቀዉ እያንዳንዱ ማህበረሰብ /በአመቻማች ባህል ዉስጥ የተዘፈቀ ማህበረሰብን ጨምሮ/ በአንድ በተወሰነ ወቅት በአንድ ወጥና ገዥ ባህል ዉስጥ ይታቀፋል። በዚህ አቃፊ ባህል ዉስጥም በርካታ የጋራ እሴቶች / common values/ መኖራቸዉ እሙን ነዉ። ከእነዚህ በርካታ የጋራ እሴቶች ዉስጥ ግን በአዎንታዊነት ወይም በአሉታዊነት ገዥ ሆነዉ የሚወጡት ጥቂት እሴቶች ናቸዉ።

የማህበረሰብን የጋራ እሴት ፈልጎ ፣አስሶና ተንትኖ በማዉጣት ሂደት ዉስጥ ከፍተኛዉ ፈተና ሆኖ የሚጋረጠዉ ግን አሁን በማህበረሰቡ ዉስጥ በገዥነት ያሉትን እያንዳንዱን እሴት ከአለፈዉ ዘመን የጋራ እሴት ጋር ያለማምታታት ነቅሶና አበጥሮ የማዉጣት ሂደቱ ጭምር ነዉ። ለምሳሌ ከዛሬ ሀያ፣ ሰላሳና አርባ አመት በፊት እዉነት፣ እርስ በእርስ መተሳሰብ፣ እምነት፣ ጀግንነትና የሀገር ፍቅር ዋነኛ የጋራ እሴቱ የነበሩ ማህበረሰብ ዛሬም እነዚህን ጉዳዮች እንደ ዋና የጋራ እሴት በጉያዉ ቀብሮአቸዉ ሊገኝም ላይገኝም ይችላል። በአሻሚና በአምታች መልኩ ይሄ ሁኔታ ሲተነተን አንዱን ተንታኝ እነዚህ እሴቶች በዚህ ማህበረሰብ ዉስጥ አሁን ድረስ አሉ የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ሲያደርጉት ሌላዉ ተንታኝ ግን የለም እነዚህ እሴቶች በሌላና በአዳዲስ ገዥ እሴቶች ተተክተዋል ሆኖም ላይ ላዩን ብቻ አሁን የማህበረሰቡ እሴት የሆኑ ይመስላል ሲል የራሱን ድምዳሜ ይዞ ሊመጣ ይችላል።

ይሄ አይነቱ ዉስብስብነት የሚስተዋለዉም አሁን ያለዉ ሁኔታ በራሱ በጥልቀት ካልተተነተነ በአንድ ወቅት ገናና የነበረ ገዥና የጋራ የነበረ እሴት አሁን ድረስ ላይ ላዩን ሲታይ ቀጣይ እሴት ሆኖ የሚገኝ የሚመስል ፣ በጥልቀት ሲመረመር ግን እየሞተ ያለ እሴትን መዞ የማዉጣት ስህተትም ሊገጥም ስለሚችል ነዉ። ከዚህም በላይ የዚህ መሰሉ እሴት አሁን ካለዉ አጠቃለይ የማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ጋር በምን ዉልና ክር እንደሚተሳሰር ለማወቅ ዉስብስብ ጉዳዮችን ያግተለተለ ዉቃያኖስ ዉስጥ እጅን ከቶና አሳዉን አንቆ የማዉጣትን ያህልም ጥረት አስፈላጊ መሆኑም ሌላዉ ጉዳይ ነዉ።

ለምሳሌም አንዳንድ ፖለቲከኞች አሁን አላራምድ ያላቸዉን የማህበረሰቡን የጋራ እሴት ያወገዙ እየመሰላቸዉ የሚያነጣጥሩት ቀስት አቅጣጫዉን ስቶ ከሞተዉንና ከጥንታዊ ማህበረሰባዊ እሴት ጋር ሲተጋገሉ በከንቱ ጊዜና ጉልበታቸዉን ሲጨርሱ ይስተዋላል። ይሄም የሚስተዋለዉ የቀደመዉን ታሪክንና በእሱ ዉስጥ ታቅፈዉ የነበሩ የዚያ ዘመን የማህበረሰቡን የጋራ እሴቶች አሁን ካለዉ የፖለቲካ ኩነት ጋር አስተሳስሮ ለመተንተን ብሎም ለዚህኛዉ ዘመን የፖለቲካ

ኩነት ፍች ፍለጋ በሚደርጉት በጎዶሎ እዉቀት ላይ በተንተራሰ ትንታኔአቸዉ ሂደት ዉስጥ ሲሆን ከዚህ አካሄዳቸዉም የሚስተዋለዉ ዕጸጽ ከላይ ላነሳንዉ ነጥብ ተጠቃሽ ማሳያና ማገናዘቢያ ሊሆነን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም ከማህበረሰቡ ዉስጥ ገዥ የሆነዉን ወርቃማ የጋራ እሴት መዞ የማዉጣት ሂደት ይበልጥ ዉስብስብና አስቸጋሪ የሚያደርገዉ ብሎም አዎንታዊ የሆነዉን እሴት ነጥሎ በማዉጣት በእርሱ ላይ ስራ መስራት የሚለዉን ህሳቤ ፈታኝ የሚያደርገዉ ሁኔታ ማህበረሰብ ሁል ጊዜም ቢሆን በሚታይም ሆነ በማይታይ መልኩ በመደብ ተከፋፍሎ መገኘቱ ነዉ። እያንዳንዱ ግልጽ ወይም ስዉር መደብም የማህበረሰቡን አጠቃላይ ሂደትና እንቅስቃሴ በመወሰን ሂደት ዉስጥ የራሱን ሚና ይጫወታል። በዚህ የመደብ ተጽዕኖ ሂደት ዉስጥ በብዙሃኑ የተያዘ የጋራ እሴት ወይም ጥቂት ቁጥር ባለዉ መደብ የተያዘ የጋራ እሴት አጠቃላይ የማህበረሰቡን እድል በመወሰን ይበልጥ ሚና አለዉ ተብሎ በአንድ እይታና ድምጽ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም።

ይህም ማለት ምናልባትም የማህበረሰቡን አጠቃላይ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚወስነዉና ያስተሳሰረዉ የጋራ እሴት ጥቂት ቁጥር ባለዉ የመደብ ሀይል እጅ ሆኖ የማህበረሰቡን ባህላዊ እንቅስቃሴና ሁለንተናዊ ሂደት የሚወስነዉ ደግሞ በብዙሃኑ መደብ ስር ያለዉ የጋራ እሴት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ወይም ደግሞ እነዚህ ሁለት እሴቶች በመስተጋብር የሚፈጥሩትም ሁኔታ ሊሆን ይችላል ገዥ ሆኖ የሚወጣዉ።

 

በአጠቃላይ ግን በአመቻማች ባህል ዉስጥ የተዘፈቀን ማህበረሰብ ከተዘፈቀበት አረንቋ መዞ ለማዉጣት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ወርቃማና አዎንታዊ የሆኑ የጋራ እሴቶችን ከማህበረሰቡ ዉስጥ ፈልቅቆና በርብሮ ማዉጣት ወሳኝና ቁልፍ እርምጃ ነዉ። ይሄን ስራ ግን በቀላልና በዘፈቀዳዊ አካሄድ መስራት እንደማይቻል ከላይ በተነሱት ነጥቦች በጥቂቱም ቢሆን ለማሳዬት ተሞክሮአል።

 

ለምሆኑ ተፈልቅቆ የሚወጣዉን ወርቃማና አዎንታዊ የጋራ እሴት በምን መልክ ጥቅም ላይ በማዋል ነዉ አመቻማች ባህልን ሰብሮ መዉጣት የሚቻለዉ? ከዚሁ ጋርስ ሊተሳሰሩ የሚገባቸዉ ሌሎች አማራጮችስ ምንድን ሊሆኑ ይችላሉ? በክፍል ሶስት የግል እይታዬን እቀጥላሉሁ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.