በአመቻማች ባህል ዉስጥ የሚቀረጽ ጽንፈኛ ስነልቦና ዲሞክራሲያዊ እሴትን ለመገንባት አቅም አለዉ?

በአመቻማች ባህል ዉስጥ የሚቀረጽ ጽንፈኛ ስነልቦና ዲሞክራሲያዊ እሴትን ለመገንባት አቅም አለዉ? (ክፍል ሁለት)

ሸንቁጥ አየለ

ክፍል አንድ

አመቻማች ባህል ያለዉ ማህበረሰብ ሰዎች በአደባባይ ጥፋት ሲያጠፉ ጥፋት የሆነዉን ነገር በግልጽና በድፍረት አይተችም ፣ አይኮንንም። በአመቻማች ባህል ዉስጥ ከቀጥተኛ እዉነትና ከጠንካራ እዉቀት አዘል ሂስ ይልቅ የጎንዮሽ ሽሙጥ፣ የኋላ ትችትና በአላዋቂነት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ዋና እሴት ናቸዉ። ከዚህም በላይ በቃል የማይነገር ንቀትና ጥላቻ ሁሉንም ወገን በሰፊ ልቦና ለማድመጥ እድል ስለማይሰጥ መደማመጥና መከባበር በማህበረሰቡ ልቡና ዉስጥ ከቶም ቦታ የላቸዉም። በአንደበትና በምላስ ላይ ግን በርካታ አመቻማች ንግግሮች በግንባር ይደመጣሉ። ማህበረሰቡ ላይ ላዩን ሲታይ የሚደማመጥና የሚግባባ ይመስላል። አንዱ አንዱንም የሚቀበልና የጋራ ቁርኝት ያለ ይመስላል። ይሄ የአመቻማች ባህል ዉቻዊ ገጽታ ግን ወደ እዉነታዉና ወደ ጥልቁ ገባ ብለዉ ለሚመረምሩ አስተዋዮች የአመቻማች ባህልን የሁለትነት ገጽታ አብጠርጥሮ ከመረዳት አያግዳቸዉም።

 

በአመቻማች ባህል ዉስጥ እዉነት ወዳዶች፣ ጠንካራ እና ጎበዝ የሆኑ ሰዎች በአደባባይ አይመሰገኑም። በዝምታ በሆድ ግን ጀግንነታቸዉ ይታሰብላቸዋል። አስገራሚዉ እና በተቃርኖ የተሞላዉ ኩነት ግን በአደባባይ እዉነተኞች፣ ጀግኖችና አዋቂዎች በአመቻማች ባህል ዉስጥ ስለማይመሰገኑ ለሃሜት፣ለአሉባልታና ለአሉታዊ ጥቃትም በስገፋት የሚጋለጡት እነዚሁ የማህበረሰቡ እንቁዎች ናቸዉ።

 

‘Some goals are so worthy, it’s glorious even to fail’ አንዳንድ ግቦች ከፍታቸዉ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ሞክሮ መዉደቅ እንኳን ወርቃማ ታሪክ ነዉ የሚለዉን ጥልቅ የሰዉ ልጅ የአስተዉሎት ፍልስፍና እንዲሁም የሀያላን ማህበረሰብ ወርቃማ መርህ አመቻማች ባህሎች ዉስጥ መተግበርና የህይወት መርህ ማድረግ በግለሰቦች ህይወት ዉስጥ ከፍ ያለ ፈተና ከመሆኑም በላይ ዋጋ ያስከፍላል። ለምን ቢባል አመቻማች ባህሎች ከፍታቸዉ ከፍ ያለ ግቦችን ለመሞከር ብሎም የሙከራዉን ዉድቀት ለመሸከም የሚያስችል አቅምም ፍላጎትም የላቸዉም እና ነዉ።

 

ከፍታቸዉ ከፍ ያሉ ግቦች ለማራመድ ቀጥተኛ እዉነትን በተላበሰ መልክ በእዉቀት ላይ/ወይም በተጨባጭ ሙከራ ላይ/ ተመስርቶ ማህበረሰባዊ ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉ ድርጊቶችን መከወንን ይጠይቃል እና አመቻማች ባህሎች ደግሞ ገና ከእንጭጩ የቀጥተኛ እዉነትን እንዲሁም በተጨባጭ ሙከራ የሚተገበሩ እዉቀት አመንጭ/አፍላቂ የሆኑ ሁነቶችን/ድርጊቶችን ሁሉ በመኮነን የጓዳዉን ሽሙጥ ፣ ሀሜትና ሽርደዳ ስልሚያበረታቱ ለግልጻዊ እሴቶች/ዲሞክራሲያዊ ጭብጦች/ ግንባታ ዋጋም ሆነ ቦታ ያሳጣሉ።

ሆኖም አመቻማች ባህሎች ዉስጥ የታሸገዉ/የታመቀዉ/ ተቃርኖና ልዩነት አደባባይ ወጥቶ በቀጥተኛ መድረክ/ ሙግትና የሃሳብ ፍጭት ስለማይደረግበት በዝምታ ዉስጥ አለመግባባት የዚህ መሰሉ ማህበረሰብ ዋና እሴቱ ነዉ። በዝምታ ፣ በታፈነ ድምጽና በማይነገር የሃሳብ ልዩነት የማይግባባ ማህበረሰባዊ ግንኙነት የአመቻማች ባህሎች መገለጫ እሴቶች መሆናቸዉ ብቻ ሳይሆን ክፋቱ በዚህ መሰል ባህል ዉስጥ ያለዉ ስነልቦና በጽንፍና በመራራ ንቀት የተሞላ መሆኑ ነዉ።

 

በጽንፍና በመራራ ንቀት ላይ የተገነባ ስነልቦና ለግልጽ ነገሮች ከፍተኛ ጥላቻንና ንቀትን በማንጸባረቅ በስዉሩ አለም ዉስጥ ግን አንዳች የተለዬ ክህሎትና እዉቀት እንዳለ ሁሉ በጉራና በማስመሰል ሌላዉን ወገን ሁሉ ይንቃል። እንደዚህ አይነት ባህሎች ለአድማ፣ ለቡድናዊነትና ለተባበረ ቡድናዊ እኩይ ስራዎች ፈጣኖችና ከብረት የጠነከረ የመተባበር ህሳቤዎችንና ፍርሃቶችን በዉስጣቸዉ አጉረዉና አጭቀዉ ይገኛሉ። አመቻማች ባህሎች መሰረታዊ መመሪያቸዉ ፈሪዎች፣ አድርባዮች እና አስመሳዮች ብለህና ዉጤታማ ህይወትን የሚመሩ ሰዎች ናቸዉ የሚል ታሳቢ ላይ ስለቆመ ለእዉቀትና ለጀግንነት ዝቅ ያለ ዋጋን ሰፍረዉ ያስቀመጡ ስንኩል ባህል ስለሆኑ የእዉነትን፣የእዉቀትን እና የጀግንነት እሴትን ለመግደል ፈጣን እርምጃን ይወስዳሉ።

 

በአመቻማች ባህሎች ዉስጥ የሚበቅለዉ የስነልቦና ጽንፈኝነት ሌላዉን ለማድመጥም ሆነ እሌሎች ጋ ዋጋ ያለዉ ማህበራዊ ጭብጥ አለ ብሎ ለማሰብ በእጅጉ ይቸገራል። ለዉይይትም ሆነ በጋራ ከፍታቸዉ ከፍ ወዳለ ማህበራዊ ግቦች ለመጓዝ በተለያዬ አቅጣጫ የሚጎትቱ ጽንፈኛ የስነልቦና ጭብጦች በአብዛኛዉ የማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ሰፍኖ ይገኛል።

 

ስለሆነም የተሻለ ዸረጃ ላይ በሀብትም ሆነ በስልጣን የደረሰዉ ወገንም ሆነ ጊዜን አድብቶ የሚጠብቀዉ ዝቅተኛዉ ወገን በተመሳሳይ የስነልቦና ጽንፍ ላይ ተንጠልጥሎ የሚገኝ ስብዕናን ያነገበ ሆኖ ይገኛል። በጽንፍ ላይ ለተንጠለጠለ ስነልቦና ደግሞ የእርስ በእርስ ማህበረሰባዊ ፍቅር፣ እዉቀት፣ ግልጽነት፣ እዉነት፣ ዉይይት፣ መቻቻል፣ ነገን በጋራ መኖር፣ ለመጭዉ ትዉልድ የጋራ ህልዉና በጋራ መጨነቅ፣ በህግና በስርአት የሚመራ ቀጣይነት ያለዉ ማህበረሰብን ለመገንባት አስተማማኝ ተቋማትን መገንባት የሚሉትና መሰል ታላላቅ የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እሴቶች የቃላት ጨዋታ እንጅ የመርህ ስራዎች አይሆኑለትም። ለጽንፈኛ ስነልቦና እነዚህ የዲሞክራሲያዊ ጥልቅ እሴቶች በአንደበት የሚነገሩ ተራ የቃላት ጨዋታ ናቸዉ እንጅ በመርህ ደረጃ የሚጠሉ መራራ እሴት ናቸዉ።

 

ለዚህም ነዉ በአመቻማች ባህል ዉስጥ የሚቀረጽ ጽንፈኛ ስነልቦና ዲሞክራሲያዊ እሴትን ለመገንባት አቅም አለዉ? በዚህ አይነት የስነልቦና ጠገግና ጥላ ስር የሚመላለስ ማህበረሰብስ የድሞክራሲን እሴት በሰለጠነዉ አለም ህሳቤና መርህ መሰረት ሊረዳዉ ይችላል ? የሚለዉ ጥያቄ ሲነሳ ፊታችንን በመዳፋች ሸፍነን አዎም ሆነ አይደም ለማለት የምንቸገረዉ ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.