ታሪክ ከፖለቲካ ትንታኔ ጋር ተሳክሮ መተንተን ከጀመረ አደገኛ ስህተቶችን መዉለዱ አይቀርም፤ አጼ ቴዎድሮስን እንደ መንደር

ሸንቁጥ አየለ

ይህ ጽሁፍ አሌክሳንደር/መልካምሰዉ/ “የፕሮፌሰር መስፍን ትልቅ ስህትተ” በሚል እርዕስ ፕሮፌሰሩ በቅርቡ በጻፉት መጽሃፍ አጼ ቴዎድሮስን በጨካ ንጉስ መስለዉ ይሄንንም የንጉሱን ጨካኝ ባህሪ ከኢትዮጵያዊ የስልጣን ስነልቦናና ባህል ጋር በማመቻመችና የዘመኑን የፖለቲካ ኩነት ከዚሁ የባህል ስር ጋር ጎትቶ በማቆራኘት ለመተንተን ያቀረቡትን አካሄድ የተቃወመበትን ጽሁፍ መሰረት በማድረግ የቀረበ ነዉ።

የተወደድከዉ አሌክሳንደር/መልካምሰዉ/ ጽሁፍህን አነበብኩት። ለመጻፍ በመነሳሳትህ ልትመሰገን ይገባሃል። በፕሮፌሰር መስፍን ጽሁፍም የተናደድክ ትመስላለህ። መናደድህም ጥሩ ነዉ። በዚህ ዘመን ታሪክ አንብቦ ታሪክ ተዛባ ብሎ የሚናደድ ሰዉም መገኘቱ ጥሩ ነዉ። ጮክ ብለዉ የሚናደዱ በርካቶች ግን ገና እንደሌሉን አንተም እኔም ያስተዋልን መሰለኝ።

በመቀጠል ግን የምሰጥህ ሀሳብ ቢኖር የፕሮፌሰርን ጽሁፍ ለመቃዎም ስለተነሳህ እራስህን ተችተህ የተነሳህበት አስተሳሰብ ልክ አልመሰለኝም። ሲጀምር እራስህን በምንም መልኩ ከፕሮፌሰር መስፍን እበልጣለሁ ወይም አንሳለሁ ብለህ ወደ ንጽጽር በመመግባት አንተ የፕሮፌሰሩን ሃሳብ መቃወምህን እንደ ትልቅ ጉዳይ አድርገህ ያህን ያህል እራስህን መኮነን የለብህም። አንተና ፕሮፌሰር የምትለያዩበት መሰረታዊ የዘመን ልዩነት ብቻ አይደለም። መሰረታዊ የሰብዕና ልዩነትም አለ። ስለዚህ ከፕሮፌሰር የሚመችህን ሃሳብ ብቻ ዉሰድ ፣ ያልተመቸህን ወደጎን በለዉ አለዚያም አሁን እንዳደረግህዉ ተቃዉመህ የመሰለህን ጻፍ። በእሳቸዉ ሀሳብ ላይ የተቃዉሞ ሀሳብህን መሰንዘርህ ብቻ የእሳቸዉን ስራ መናቅህና የእሳቸዉን የአገር ጥላነት ጥያቄ ዉስጥ ማስገባትህ ነዉ ማለት አይደለም። ማንም አሌ ማለት እንደማይችለዉ ፕሮፌሰር መስፍን በነጻ ህሳቤአቸዉ በርካታ መጽሃፍትን በመጻፍ በርካታ እዉቀትን ለትዉልዱ የዘሩ ምሁር ናቸዉና። ከሁሉም በላይ ምሁር የሚለዉን መስፈርት በዋናነት ያሟሉት የመሰላቸዉን ሀሳብ በማራመድና በርካት የትዉልድን አዕምሮ ለተጠይቅ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን በማቅረብ ጭምርም ነዉ።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለአንደ የግል ጋዜጣ ጽሁፌን ልኬዉ ሃሳቤን አላስተናገዱልኝም ያልከዉንም እርሳዉ። የእኛ አገር የዲሞክራሲ አስተሳሰብ አስቂኝ ህሳቤን ከኋላዉ ያነገበ ስለሆነ ስለግል ጋዜጦችም ያንተን ሃሳብ ማስተናገድና አለማስተናገዳቸዉን እንደ ቁም ነገር አትዉሰደዉ። እኛ አገር ዲሞክራት ነኝ የሚልህ ሰዉ ዲሞክራሲ ማለት እሱ የሚያስበዉ አስተሳሰብ ብቻ ቅቡል ነዉ ብለህ ካላልከዉ በጸረ ምናምን እነት ሊፈርጅህ ዝግጁ ነዉ። አንተን የገጠመህ እዳ ፕሮፌሰር መስፍንንም ሆነ ሌሎቻችንንም ከግል ጋዜጦች ስላለመግጠሙ ምን መረጃ አለህ? አንድ ሰሞን ሊብራን ነን ያሉን የግል ጋዜጦች ስንት ሃሳቦቻችንን አፍነዉ እንዳስቀሩት ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጽ አለብን? ብንገልጸዉም ባንገልጸዉም ምንም ትርጉም የለዉም። ሀሳብ የማህበረሰብ መሰረት ባልሆነበት ሁኔታ ሁሉንም ሀሳብ ማባከን ምን የሚለዉጥ ይመስልሃል?

ወደ ዋና ነጥቤ ስገባ አንተ በጣም ተብከንክነህና አምርረህ ፕሮፌሰር መስፍን የሰሩትን ስህተት ከወቀስህ ብኋላ ደግሞ አንተም ተመልሰህ እንደሳቸዉ ስህተት ወደ መስራት ገባህ። ለምን ብትል አንተም ፖለቲካዉን እና ታሪኩን እያነጻጸርህ መተንተን ጀመርህና ከሁለት መቶ አመት በፊት የነበረዉን ኩነት ከዚህ ዘመን ኩነት ጋር ጎትተህ በማምጣት ዘመናትን በገመድ ጎትቶ ማቀራረብ ይቻል ይመስል በአንድ ትሪ ላይ አስቀምጠህ መስፈርና መተንተን ጀመርህ።

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የስልጣን ስነልቦና እና የባህላዊ የስልጣን ህሳቤን ለመተንተን ያግዘኛል ብለዉ የሁለት መቶ አመት ሁኔታን ከዛሬ ዘመን ጋር ቀላቅለዉና አዋህደዉ ለመተንተን ሲነሱ በርካታ መሰረታዊ ነጥቦችን ሳቱ። በአጼ ተዎድሮስ ታሪክ ዙሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሃፊያን ሁለት ሃሳቦችን ባንድ ጊዜ ሲያራምዱ ይስተዋላሉ። አንደኛዉ አጼ ቴዎድሮስ ደግ፣ሩህሩህ፣አስተዋይና የአንዲት ኢትዮጵያን መሰረት ለማምጣት በጥልቀት የማሰኑ መሪ መሆናቸዉን ሲያቀርብልን ሁለተኞቹ ደግሞ የአንዲት ኢትዮጵያን መሰረት ለማምጣት በጥልቀት የማሰኑ መሪ መሆናቸዉን ተቀብሎ ግን ጨካኝና ርህራሄ የማያዉቁ መሪ መሆናቸዉን የሚያናፍሱ ወገኖች አሉ። ፕሮፌሰር መስፍን የመረጡት ታዲያ የአንዲት ኢትዮጵያን መሰረት ለማምጣት በጥልቀት የማሰኑ መሪ መሆናቸዉን ተቀብለዉ ግን ጨካኝና ርህራሄ የማያዉቁ መሪ ናቸዉ የሚሉ ወገኖችን አስተሳሰብ በማራመድ የኢትዮጵያን የባህል አገዛዝ እሴት ለመተንተን ወደዚህኛዉ ዘመን አጤ ቴዎድሮስን ጎትቶ በማምጣት የተወነጋገረ ትንታኔ መስጠትን መርጠዋል። የፖለቲካ ትንታኔ ለመስጠት ሁለት መቶና የመቶ አመታት የታሪክ

ኩነቶችን በጥቂት ቃላት ሸቅቦና አንሸዋሮ በማቅረብ እንዘጭ እንቦጭ /በራሳቸዉ በፕሮፌሰር ቋንቋ/ የሚባልበት አገር ቢኖር የእኛ አገር ብቻ ነዉ።

ፖለቲካ በአንድ ዘመን በሚፈጠር የፖለቲካ ማህበረሰብ አስተሳሰብና ስርአት ለመመራትና ለመተዳደር የሚከተለዉ የየዘመኑ ህግና ስርአትን መሰረት አድርጎ የሚዘወርበት ርዕዮት አለም መነሻና መድረሻዉ በዋናነት ዘመኑ እራሱ መሆኑ እሙን እና ቅቡል ሆኖ ሳለ የእኛ ተንታኞች የባህል መሰረትና ስነልቦናችንን ለማኮሰስና ለመዉቀስ /ይሄ ማንነታችንን የማኮሰስ አካሄድ የፕሮፌሰር መስፍን አጀንዳይሆናል ብዬ አላምንም/ ወደ ቀደሙ ዘመናት መሪዎችና ታሪኮች ያለ ጥልቅ ትንታኔና ህሳቤ ዘዉ ብለዉ ገብተዉ እንተፍ እንተፍ ብለዉ ያለምንም ይሉኝታና ሀይ ባይ ያን ዘመን አበሸቃቅጠዉት ይወጣሉ:: ማወቅህን ለማሳወቅ ያለ ምንም ክብር ያን ዘመን ማንኳሰስ ከፍ ያለ የተንታኝነትህን ብቃት ማረጋገጫ ሆኖ የሚታይበት አገር የት መሰለህ? እዚህ እኔና አንተ ትዉልድ ሀገር ዉስጥ ነዉ።

በመላዉ አለም ከሁለት መቶ አመት በፊት የነበረዉ የስልጣን መወጣጫ ህሳቤና ስልት በጦርነት ጠላትን ማንበርከክ ብቻ እንደነበረ መዘንጋታቸዉና በመላዉ አዉሮፓና ሌሎች አካባቢዎች እንደነ ናፖሊዮን ፣ ቢስማርክ የመሳሰሉ ጦረኛ መሪዎች ጠላቶቻቸዉን እጭ ምጭጭ ያደረጉትና ሀገራቸዉን ያዋሃዱት በጠነከረዉ ወታደራዊ ስርአታቸዉና በመራራዉ ቅጣታቸዉ መሆኑን ሳያገናዝቡ የአጼ ቴዎድሮስን ጨካኝነት ለማጉላት ሲሉ የዚህን እጅ ቆረጠ እነዚያን አንገት ቀላ ይሄም የሚያሳዬዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ የስልጣን መሰረቱ ሀይልና ዱላ ነዉ ሲሉ ይደመድማሉ። ለምሆኑ በዚያን ዘመን አጼ ቴዎድሮስ ከሸዋ ጦረኞች ጋር ፣ ከጎጃም ጦረኞች ጋር ፣ ከወሎ ጦረኞች ጋር ፣ ከትግራይ ጦረኞች ጋር ተደራደረዉ የኢትዮጵያን አንድነት ማምጣት ይችሉ ነበር? ፕሮፌሰር እንዲህ አስበዉ ከሆነ ፕሮፌሰሩ የፊዉዳሎችን የጦረኝነት እና የሀይለኝነት ባህሪ አሁን አለም ከደረሰበት የዲሞክራሲ ህሳቤ ጋራ የማቀላቀል ስህተት እየሰሩ ነዉ ማለት ነዉ።

የዚያ ዘመን ታሪክ፣ የባህል እሴትና የስልጣን መሰረት ዋና ስልቱና ቅኝቱ በጦርነት ማሸነፍ ነበርና አጼ ቴዎድሮስ ከዚህ የተለዬ ነገር አላደረጉም ነበር። አጼ ቴዎድሮስ ከዘመነ መሳፍንት ጀምረዉ የኢትዮጵያን ግዛት ተከፋፍለዉ ትንንሽ ነገስታት ሆነዉ ለአንዲት ኢትዮጵያ መፈጠር እንቅፋት የሆኑን መሳፍንቶች በጦር መደምሰሳቸዉ፣ የዘመኑን ቅጣት መቅጣታቸዉ በዚህ ዘመን ላይ ቆመን ስህተት ነበር፣ትክክል ነበር እያሉ በዚህኛዉ ዘመን የእሴት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ለመተንተን እና ቴዎድሮስን ጨካኝ መሪ ብሎ ለመፈረጅ መነሳት መሰረታዊ የታሪክ ህጸጽን ያነገበ አካሄድ ነዉ። እንዲሁም አጼ ቴዎድሮስን ለማበሳጨትና በእሳቸዉ ላይ ተንኮል ለመጎንጎን ከዚህም ሆነ ከዚያ አቅጣጫ በሚዶሉቱ ወገኖች ላይ መራራ ቅጣት መዉሰዳቸዉን መዞ በማዉጣት እንደ አንድ የኢትዮጵያ የባህል መሰረት መዉሰድና ያን ድርጊት ከዚህኛዉ ዘመን ጋር ጎትቶ ለማገናኘት መሞከርም መሰረታዊ የጠተይቅ አካሄድን አያሟላም።

የቴዎድሮስን መሰረታዊ የግለ ሰብዕና ዉቅረት፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ የእምነት ጭብጥና የስልጣን መወጣጫ ስልቶች አንድ ላይ ጨፍልቆና አንድ ድርጊት በዬትኛዉ እሴት ላይ በመሰረታዊነት ተመስርቶ እንደተከሰት ሳይተነትኑ በጥቅልና በጅምላ የኢትዮጵያን ባህል ወይም እምነት ወይም አንድ ነገር ነቅሶ በማዉጣት ከድርጊቶች ጋር ሁሉ ለማመቻመች መሞከሩ ስህትት ትንታኔን ማስከተሉ እሙን ነዉ። ለምን?

በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ነገስታትና ሃያላን ሰዎች የእርስ በእርስ መጠፋፋትን ለማስቀረት ሲሉ ከአንደኛዉ ወገን ወደሌላኛዉ ወገን ስልጣንን በፈቃዳቸዉ ያሸጋገሩበት ወቅት ነበር። ይሄም የድርድር ስልትና ጥበብ ሀያሉ ስልጣኑን ይዞ እንዲቀጥል ሲያስችለዉ ደካማዉም ቢያንስ በሃያሉ ህልዉናዉ ሳይደመሰስ የህልዉና ዋስትና አግኝቶ እንዲቀጥል እድልን ሰጥቶታል። ለምሳሌም የሰለሞናዉያንን እና የዛግዌ ነገስታትን ዉልና ድርድር ማስታወሱ በቂ ነዉ። ይህ የኢትዮጵያ ታሪከ አንዱ ገጽታና የባህላዊ የስልጣን ስር ነዉ። ሌላም ታሪካዊ ክስተት መዞ ማምጣት ይቻላል። አጼ ዮሐንስና ዐጼ ሚኒሊክ በስልጣን ባልተግባቡ ጊዜና ጦር ለመማዘዝ በተቃረቡ ጊዜ ሊመዘዝ የነበረዉ ጦር በድርድር ወደ አፎቱ እንዲገባ ተደርጎአል። የሁለቱ ንጉሶች ድርድር ሁለት ሶስት ጊዜ እየተደረገ የቀረዉ ጦርነትና እርስ በእርሳቸዉ ሳይጠፋፉ የሃይል ሚዛናቸዉን ሁለቱም ጠብቀዉ የተጓዙበት የድርድር ታሪክም በራሱ አንዱ የኢትዮጵያ ገጽታ ነዉ።

ፕሮፌሰር መስፍንም ሆኑ ሌሎች ጸሃፊዎች ይሄንም የታሪክ ክፍል ማንሳት አይፈልጉም ። ምክንያቱም ያለፈዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ለመኮነን ስለማያመቻቸዉ ነዉ። ሌሎች ደግሞ ይሄን የሃይለኞች ድርድርና ያለመጠፋፋት ጥበብ ከተንኮልና ከሸር ጋር ሊያያይዙት እንቶፍ እንቶፍ ሲሉ ይስተዋላሉ። በተለይ አንዳንዶች ነብሳቸዉም ሆነች አዕምሮአቸዉ የኢትዮጵያን ታሪክ ከስህተት፣ ከተንኮልና ከሸፍጥ ጋር ለማቆራኘት ከፍተኛ የፈጠራ ስራዎችን የሚያጠነጥኑበት ዘመን ነዉ። ቁልጭ ያለዉ ሚስጥርና እዉነት ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አንዳንድ ጊዜ ለስልጣን የሚሻኮቱ ሀያላን ጦረኞች የሃይል ሚዛናቸዉን እያመዛዘኑ ወደ አዉዳሚና ሁል አቀፍ ጦርነት ከመግባት ይልቅ በድርድር የስልጣን ሽግግር ያደርጉ እንደነበረና ይሄም

አንዱ የታሪካችን አካል መሆኑን ማስተዋል አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል እንጅ ሌላ ትርጉም አሰሳ መሄድ አስፈላጊ እንዳልሆነ ነዉ። ሆኖም እዚህ ጋ የሚነሳ ጥያቄ አለ። ይሄ አይነት የድርድር አካሄድ ከባህላችን የተነሳ ነዉ ወይስ ከግለሰቦች ሰብዕና የተነሳ ነዉ ? ነዉ ወይስ እምነት የተጫወተዉ ሚና ነዉ? የሚለዉ ጥያቄ ነዉ። ይሄ አይነት ጥያቄ በዘፈቀደ ሳይሆን በጥንቃቄ በሰፊ መረጃ ላይ ተንተርሶ በጥናት ሊመለስ የሚገባዉ እንጅ አሁን አንዳንዶች እንደሚያደርጉት አንዱን የድርጊት ጭራ ብቻ ጨብጦ ከዉስጥ ያለዉ ዉስብስብ የድርጊቱ መስፈንጠሪያዎችን ሳያስሱ ፈጥኖ መደምደም አግባብ አይደለም።

ሌላም የታሪክ ክፍል አለን። ይሄዉም ነገስታት በራሳቸዉ ፈቃድ በመነሳት ስልጣን በመልቀቅ ሌላ የሚሆናችሁን ተኩ እኔ እግዚአብሄርን ማገልገል እፈልጋለሁ እያሉ ከሃላፊነት በራሳቸዉ ፈቃድ የሚነሱበት የታሪክ ክስተቶችንም ያስመዘገብን ህዝብ ነዉ። ይሄሰ/ የባህላችን ዉጤት ነዉ? የእምነታችን ዉጤት ነዉ? የግለሰቦቹ ተክለሰብዕና ነዉ? ነዉ ወይስ የሌላ ጉዳይ ጫና ነዉ? ነዉ ወይስ የነዙህ ሁሉ ጉዳዮች ድምር ዉጤት ነዉ? አንዚህ ጉዳዮች ሳይመለሱ አንድ የኢትዮጵያን ንጉስ ድርጊት /ያዉም እጅግ እሩቅ ዘመን በነበረ ሁኔታ ዉስጥ የተከናወነን ድርጊት/ መዞ በማዉጣት ባህላችን ወይም እምነታችን እንዲህ ስለሆነ በማለት የዚያን ዘመን የድርጊት መሰረት ከዚህኛዉ ዘመን የድርጊት መሰረት ጋር በግድ ለማዋሃድ መሞከር የሚመራን ወደ ስህተት ድምዳሜ ነዉ።

እንግዲህ የኢትዮጵያን ባህላዊና ታሪካዊ የስልጣን እሴት ለመተንተን አንዱን ክስተት ብቻ መዞ ለወቀሳ ብቻ መንደርደርና በዚህ የታሪካዊና ባህላዊ ትንታኔ ላይ ተመስርቶ ባህላዊ የዘመኑን ፖለቲካ ለመተንተን መወራጨት በራሱ በርካት እጸጾችን አስከትሎ መንጓተቱ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ከእጸጾቹም አንዱ በታሪክ ዉስጥ ያለፉ ግለሰቦችን ሰብአዊ ጭብጥና ግለሰበአዊ እሴት በመርሳትና በማኮሰስ በግለሰቦች የግል ባህሪ የመጣን የታሪክ ድርጊት ወደ ባህላዊ ስር ወይም ወደ እምነት ህሳቤ የማጣበቅ አባዜን ማስከተሉ ነዉ።

ይሄን አባባል ለማረጋገጥ የዘመናችን ትዉልድ አዕምሮአችን ከታጠበበት እና እንደ ተምሳሌት ከምንወስደዉ የአሜሪካኖች ታሪክ ምሳሌ እንጥቀስ። የመጀመሪያዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆርጅ ዋሽንግተን ከሁለት ጊዜ የፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመን በላይ ስልጣን አልፈልግም ብለዉ ከስልጣናቸዉ ወርደዉ ነበር። ያዉም እንዲቀጥሉ ሲለመኑ። ከእሳቸዉ ብኋላም የመጡ ፕሬዝዳንቶች አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ እየተመረጡ ስልጣንን ወደ ሌሎች ሲያስተላልፉ ነበር። ሆኖም 32ኛዉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት /Franklin Delano Roosevelt / አራት ጊዜ ሲመረጡ ስልጣኑን ዝም ብለዉ መቀጠልን መርጠዉ ነበር። አሁን ጥያቄ እናንሳ ። ይሄ የባህል ተጽእኖ ነዉ ወይስ የሰዉዬዉ የግለሰብዕና ተጸዕኖ? መልሱ ቀላል ነዉ። የግለሰቡ የግለሰበአዊ ሰብዕና ያስከተለዉ አካሄድ ነዉ። ብልጦቹ አሜሪካኖች ታዲያ ሰዉዬዉን ከመኮነን ይልቅ ፣ ወይም ባህላቸዉን ከማበሻቀጥ ይልቅ ያነሱት አንድ ጥያቄ የግለሰቦች የስብዕና አካሄድን ሊገታ የሚችል የስልጣን ዘመንን የሚገድብ ህገመንግስት መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግን መረጡ። እናም አደረጉት። የስልጣን ጉጉትና ጥማት ያለበት ሀይለኛ ሰዉ የሚገታዉና ለዲሞክራሲያዊ ስርአቱ የሚገብረዉ በሃያል ስርአትና በዉጤታማ ተቋማት ብቻ መሆኑን እዚህ ጋ ልብ ይሏል።

ሆኖም በእኛ ሀገር የእኛ ተንታኞች የእኛ አገር የፖለቲካ ትንታኔ ሚስጥሩ አልገባ ሲላቸዉና መዉጫ ቀዳዳ ሲጠፋቸዉ ያለፈዉን መዉቀስና የባህላችን ስር፣ የሀይማኖታችን ዝክንትል፣ የአየር ጸባያችን ተስማሚነት፣ እና ተቆጥረዉ የማያልቁ ግሳንግስ ምክንያት ድርደራ ይዘመታል። እናም በቅርቡ የተያዘዉ ፈሊጥ ደግሞ አጼ ቴዎድሮስ ጨካኝ ነበሩ ፣የእሳቸዉ ጭካኔም ከባህላችን የተወረሰ ስለሆነና የባህላችን ጭካኔም በዚሁ ስለቀጠለ ወደ ዘመናዊ የስልጣን አስተሳሰብ ለመራመድ እንቅፋት ሆነብነ ፤ ገዳይ እወዳለሁ የሚለዉ የባህላችን ምንትስ እና ምናምን ስነልቦናችን ለድርድር አመች እንዳይሆን አድርጎታል የሚሉና መሰል ትንታኔዎች ግን ፍሬ ነሩን የለቀቁ ትንታናዎች በዚህና በዚያ ብልጭ ድርግም ሲሉ ይስተዋላሉ።

የተወደድከዉ መልካም ሰዉ፤ ሆኖም አንተም ተመሳሳይ የታሪክ ትንታኔ ስህተት ወደ መስራት ገባህ ። ይሄዉም ከሁለት መቶ አመት በፊት የነበረዉን አጠቃላይ ኩነት በማይወክል መልኩ አጼ ቴዎድሮስን ጎትተህ በማምጣት ከዚህኛዉ ዘመን የፖለቲካ ተዋንያኖች ጋር የማነጻጸር ስራ ሰራህ። ታሪክ ከፖለቲካ ትንታኔ ጋር ተሳክሮ መተንተን ከጀመረ አደገኛ ስህተቶች ይወለዳሉ የሚል ነጥብንም ማንሳት የወደድሁትም ለዚህ ነዉ። ለምሆኑ የአጼ ቴዎድሮስን አስተሳሰብና ሰብዕና በምን መስፈርትና መለኪያ ላይ አስቀምጠህ ነዉ ከዚህኛዉ ዘመን ፖለቲከኞች ጋር ልታወዳደር ደፋ ቀና ያልከዉ?

ያንተ ሙግት መሆን ያለበት በአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ዙሪያ እንደ ታሪክ ጭብጥ አጼ ቴዎድሮስ ደግ ንጉስ ነበሩ ወይስ ጨካኝ ንጉስ የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ መነሳት ነዉ። ይህ ጥያቄ መመለስ ያለበት በራሱ በታሪክ ማስረጃዎችና በታሪክ ትንታኔዎች ብቻ ነዉ እንጅ አሁን ካለዉ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በንጽጽር ቀርቦ አይደለም።

ፕሮፌሰር መስፍንንም ሆነ ባለፈዉ ጽሁፉ አጼ ቴዎድሮስን በጨካኝ ተምሳሌት መስሎ የኢትዮጵያን የጀግንነት ስር ባልተገባና በተዛባ መልኩ በማወሳሰብ ከዚህኛዉ ዘመን የጀግና ፍለጋ ጋር አመቻምቾ ለማቅረብ የሞከረዉን እዉቁን የወግ ጸሃፊዉን ዳንኤል ክብረትን ልትሞግታቸዉ የሚገባበት ነጥብ አጼ ቴዎድሮስ ደግ ንጉስ ነበሩ እንጅ ጨካኝ ንጉስ አይደሉም የሚለዉን የታሪክ ጭብጥ አንግበህ መሆን አለበት እላለሁ። ያንተ ሙግት መሆን ያለበት የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ አንሸዋራችሁና በጭካኔ መስላችሁ ያልሆኑትን አቅርባችኋል የሚል ህሳቤን ማንሳት ነዉ። ማስረጃዎችህን ከታሪክ ነቅሰህ ማቅረብ ትችላለህ።

እኔ በግሌ አጼ ቴዎድሮስ ቆራጥና የተዋጣላቸዉ ጀግና ነበሩ እንጅ ጨካኝ ንጉስ አልነበሩም ከሚሉት ወገኖች እወግናለሁ ። ለዚህም የታሪክ ማስረጃን አንድ ሁለት ብዬ ማቅረብ እችላለሁ። አንደኛ ቴዎድሮስ ጦርነት ገጥመዉ ካሸነፉ ብኋላ እና አንድ አካባቢ ለእሳቸዉ መገበሩን ካረጋገጡ የንጉሶቹን ዘሮች አያጠፉም፣ አካባቢዉንም አያጠፉም ነበር።የቴዎድሮስ ብቸኛ ራዕይ የተበተነዉ ህዝባቸዉ በሀይል በአንድ እንዲሰበሰብ ብቻ ነበር። ይህ የሃይል ህሳቤ ደግሞ በዘመኑ የነበረ የመላዉ አለም መሪዎች ፍቱን አማራጭ ነበር። ማረጋገጫ የሚል ካለ የሸዋዉ ምኒሊክን ልጃቸዉ አድርገዉ ይዘዉ ሄዱ ፤ የወሎ ገዥዎችን ካስገበሩ ብኋላ አንድም ሳይነኩ ተቀብለዋቸዋል። በርካታ የቴዎድሮስ ተቀናቃኞች የቴዎድሮስን የበላይነት አምነዉ ለአጼ ቴዎድሮስ ከገበሩና እጅ ከሰጡ አጼ ቴዎድሮስ የሚገባቸዉን ክብር ሰጥተዉና አሞላቀዉ ያኖሯቸዉ ነበር። ቴዎድሮስ ደግ ሩህሩህ የነበሩት ለመላዉ ህዝባቸዉ ጭምር ስለነበረ የሚያወጡዋቸዉ አዋጆችና የመተዳደሪያ ህጎች ህዝቡን እንዳይበድልባቸዉ ይጠነቀቁ ነበር። ሆኖም የቴዎድሮስን ጀግንነት የተጠራጠሩና ያንገራገሩ ወገኖች የሚቀጡት ቅጣት መራራና የማያዳግም ነበር።

ለዚህ ማሳያ የሚሆነንም ሸዋና ጎጃም አልገብር ብለዉ ከቴዎድሮስ ጋር ጦርነት ዉስጥ የገቡ ጊዜ የተቀጡት ቅጣት መራራ መሆኑ ነዉ። በዚህ ዘመን ላይ አንድ ጸሃፊ ተነስቶ የቅጣቱን መራራነት ጠቅሶ የቴዎድሮስን ጨካኝነት ለማሳዬት ከሞከረ ይሄ ጸሃፊ የዚያ ዘመን የነበረዉ ማህበራዊ ዉቅረትና አጠቃላይ የስልጣን ስነልቦናዊ መሰረት አልገባዉም ማለት ነዉ። ጦርነትና ሀይል ብቸኛዉ የስልጣን መሰረት መሆንኑ ተቀናቃኞቹ ጦረኞችም መራራ ተዋጊ እንደነበሩና ቢሳካላቸዉ ደግሞ ተመሳሳይ እርምጃ በተቀናቃናቸዉ ላይ ወስደዉ ተቀናቃኛቸዉን ከማሳመን እንደማይመለሱ አልገባዉም ማለት ነዉ። ደግሞም ይሄ እዉነትና አጠቃላይ የስልጣን መወጣጫ ስልት በኢትዮጵያ የነበሩ ጦረኞች ጋር ብቻ ይሰራ የነበረ ሳይሆን በመላዉ አለም ይሰራበት የነበረ እዉነት እና ስልት ነበር።

ዛሬ አንዳንድ ሰዎች እያሳከሩ የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ ለመኮነን ሲሉ ሽና ሽህ ሰበብና እንቶፈንቶ እየደረደሩ የቀደሙት መሪዎችን ለመዉቀስ ዲሪቶ ነገር ሲመዙና ጭብጥ አልቦ ክስ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። እንዲያዉም አንዳንዶች ታሪኩ ይከለስና ይጻፍ ብለዉ ያለ እፍረትና እዉቀት ሲናገሩም እያዳማጥን እዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ተከልሶ ቢጸፍ የአሁኑ ትዉልድ ችግሬ ናቸዉ የሚላቸዉን ችግሮቹን ሁሉ ይቀርፍ ይሆን ስንል ጠይቀናል። በአጠቃላይ ግን ሰዎች ለምን እንዲህ አሰቡ ማለት አይቻልም። አንዳንዶች እዉቀት እራሷ እየሸወደቻቸዉ፣ አንዳንዶች በየዋህነት፣ሌሎች የዘመኑ የትምህርትን እሴት ከኢትዮጵያዊ ስር ጋር ማጣጣም ሲሳናቸዉ፣ሌሎች በተንኮል፣ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያ ለሚለዉ ህሳቤ ካላቸዉ መራራ ጥላቻ ታሪኩን ጨምሮ ጠልተዉ ወዲህና ወዲያ ሲወራጩ ይተያል። ሁሉም ግን የፈለገዉን ማራመዱ ክፋት የለዉም። እንዴት ክፋት የለዉም ይባላል ? የሚል ካለም ተወደደም ተጠላም ያለንዉ በዚህ ሁሉ ዉጥንቅጥ ዉስጥ ስለሆነ ሌላ ምን ሊባል ይቻል ይሆን? የሚል ጥያቄን አንስቼ አልፋለሁ።

ዋናዉ የእዚህ ጽሁፍ ጭብጥ ግን አሁን ያለዉን የፖለቲካ ሁኔታ ለመተንተን ከታሪክ ጋር ማምታታትና ማሳከር አግባብ አይደለም የሚል ነዉ። ከታሪክ ዉስጥ እጅግ ቀጭን እና ትንሽ ክር በመምዘዝ በርካታ እና ዉስብስብ እሆነዉ እዘመኑ ፖለቲካዊ ሂደት ዉስጥ በመቀላቀልና በማሳከር አላግባብ ትንታኔን ለማሳመር መሞከር መጥፎ አካሄድ ብቻ ሳይሆን ሌላ ስህተትም የሚወልድ ነዉ። በርግጥ ከታሪክ መማር ይቻላል። ከታሪክ መማር የሚቻለዉ ግን በተግባራዊ መልክና ስርአት ባለዉ መልክ እንጅ በማይጨበጥ የማሳከርና የሽወዳ ትንታኔ አይደለም። ለምሳሌም አሜሪካኖቹ እንዳደረጉት የአንድን ገናና ሰዉ የስልጣን ጥማት መግታት የሚቻልበት ስርአትና አካሄድ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ከታሪክና ከልምድ መነሳት ይቻላል። በአንድ ወቅት በአንዲት ሀገር ዉስጥ የሚከሰት ክስተት በራሱ ከግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ፣ ወይም ከባህል፣ ወይም ከእምነት፣ ወይም ከዘመኑ ርዕዮት አለም ህሳቤ የተነሳ የተከሰተ ነዉ ወይስ ከሌላ አቅጣጫ የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ዉስብስብስብና ያልተመለሱ ተያያዥ ጉዳዮች እያሉ አንዷን ነጥብ ብቻ መዞ በአንድ ህዝብ የታሪክ ማንነት ፣ የባህል መሰረት ላይ በዘፈቀደ ተንተርሶ የዚህን ዘመን ፖለቲካ ለመተንተን መነሳት በራሱ ስህተት ባይሆንም በርካታ ጥንቃቄን ይጠይቃል።

አሁን አንድ ምሁር ጃፓን ከ1952 ዓም ብኋላ በአጭር ጊዜ የስልጣኔ እመርታን አሳይታለች። ሆኖም ይህች አገር ልክ እንደኛ አገር በቀደመዉ ዘመን በሀይለኛና በጦረኛ ንጉሶች እየተመራች ነበር ፣ ህዝቧም ልክ እንደኛ ህዝብ በንጉሶች መራራ

አገዛዝ ስር ይኖር ነበር ብሎ ቢነግርህ ከዚህ አባባል ምን አይነት ድምዳሜ/ትምህርት ታወጣለህ? እንደዉነቱ ከሆነ ከዚህ መሰል አባባል ምንም የሚወጣ ግኝትና ትምህርት የለም። ከዚህ መሰሉ አባባል አንዲት ትክክለኛ ነጥብ አንጥሮ ለማዉጣት ሰፊ ምርምርና ጥናት ማድረግን ፣ በስማ በለዉ ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ አካሄድን ፣ አድካሚና ትዕግስት አስጨራሽ ስራን ይጠይቃል። ሆኖም የሚገኘዉ ግኝት አሁን ላለህበት ችግር ምንም የሚሰጥህ መፍትሄም ላይኖር ይችላል። ምናልባት የሆነ ፍንጭ ብልጭ ያደርግልኝ ይሆን ብለህ በስፋት ልትዳክርም ትችላለህ።

እዉነታዉ ግን አሁን ያለዉ ሁኔታ በራሱ በጥልቀት ካልተተነተነ ከዚህ አንተ ከታሪክ መዘህ ያመጣህዉ እዉነት ጋር በምን ዉልና ክር እንደሚተሳሰር ለማወቅ ዉስብስብ ጉዳዮችን ያግተለተለ ዉቃያኖስ ዉስጥ እጅህን ከተህ እያማሰልህ መሆንህ ብቻ ነዉ። እናም ታሪክ ከፖለቲካ ትንታኔ ጋር ተሳክሮ መተንተን ከጀመረ አደገኛ ስህተቶችን መዉለዱ አይቀርም፤ አጼ ቴዎድሮስን እንደ ምሳሌ ብንወስድ አሁን በእሳቸዉ ዙሪያ የሚነሱና እሳቸዉን በጨካኝነት በማሳዬት ጭካኔና ዱለኝነት የባህላችን መሰረት ነዉ በሚል መንደርደሪያ ለዚህኛዉ ዘመን የፖለቲካ ኩነት ፍች ፍለጋ ወዲህና ወዲያ የሚደረጉ መወራጨቶች ብዙም አያስኬዱም የሚል ህሳቤ ያለኝም ለዚህ ነዉ። ታሪክን ለአስተምህሮትነት ፣ ለመጻኢዉ ጊዜ እርሾነትና መንደርደሪያነት እንዲሆን በምን አይነት ጠንቃቃ አካሄድ ልንቀርበዉ ይገባል የሚል ህሳቤን ማንሳት ግን ተገቢ መሆኑን አሌ አልልም።

 

ሀሳቤ ግልጽ ካልሆነ ደግሜ ለማብራራት እሞክራለሁ።

ሰላም ሁንልኝ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.