ሸዋ የኢትዮጵያ እምብርትና የታሪክ አስኩዋል

ትንሽ ስለሸዋ

በሞላ ሃበሻ

ሸዋ የኢትዮጵያ እምብርትና የታሪክ አስኩዋልና  እንደ ውቂያኖስ ውሃ ተጨልፎ ከማያልቀው ታሪክ በጥቂቱ
በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ይዳሰሳሉ።
******************************************************
ሽዋ በኢትዮጵያ ገጸ ምድር መሃል ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ነው። ለብዙ መቶ ዓመታት በሉዐላዊነት በራሱ መሪዎች ሲተዳደር የኖረ የኢትዮጵያ አካል ሲሆን፣ ርዕሰ ከተማው እስከ ፲፰፻፹፱ ዓ/ም በሰሜን ሸዋ ውስጥ በየጊዜው በተለያዩ ሥፍራዎች ሲፈራረቅ ቆይቶ ባለፉት መቶ በላይ ዓመታት ግን አዲስ አበባ ሆናለች። ደብረ ብርሃን፤ አንኮበር፤ አንጾኪያ፤ ልቼ እና እንጦጦ በተለያዩ ጊዜያት የሸዋ ርዕሰ ከተማዎች ነበሩ። የሸዋ ገጸ ምድር እምብርት ባሁኗ ኢትዮጵያ መሃል የሚገኙት ተራራዎች ናቸው። የግዛቱ ተራራማነት የተፈጥሮ መከላከያ በመሆን ከውጭ ወረራ ለመላ አገሪቱ ደጀን የነበረና በፍትህ የአስተዳደር ዝናውም ለሌላ የኢትዮጵያ ዜጋዎች መጠጊያና መሸሸጊያም ነበር፣

የዳግማዊ ምኒልክ፣ የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን ለማስታረቅ የሞከረችው ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፣ የአማርኛ ፊደል ገበታ በስፋት በማሰራጨት የሚታወቁት ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ እና የሌሎችም ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የትውልድ ስፍራ የሆነችው ሰሜን ሸዋ፤
******************
ደብረ ብርሃን
********************

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረብርሃን ከአዲስ አበባ 130 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የተቆረቆረችውና ስያሜዋን ያገኘችው ደግሞ ከ500 አመት በፊት በ1446 ዓ.ም አካባቢ በአፄ ዘርአያቆብ /1426-1460ዓ.ም/ ነበር፡፡ ከተማዋ ድሮ ደብረኢባ በመባል የምትታወቅ ሲሆን የንጉሱ የግራ በአልቴሃት /ግራ በአልቴሃት ከንጉሱ ሶስት ሚስቶች የአንደኛዋ የክብር ስም ነው/ ርስት ነበረች፡፡ በ1440ዎቹ መጀመሪያ ንጉሱ ጐብኝተዋት
ደስ ስለተሰኙባት ተጉለት የነበረውን መናገሻ ወደዚያ አዙረው የድንኳን ከተማቸውን ከተሙባት፡፡ በኋላም ቤተመንግስት አሳንፀውና ባለወርቅ ጉልላት የነበረውን የስላሴ ቤተክርስቲያን አሰርተው ቆረቆሯት፡፡ “ተአምረ ማርያም” የተሰኘ የጥንት ድርሳን የከተማዋን ስያሜ ከአንድ ተአምራዊ ሁነት ጋር አያይዞ ይገልፀዋል፡፡ በ1446 ዓ.ም በክርስትና ሃይማኖት ካህናትና በጥቂት የሃይማኖቱ ተከራካሪዎች መካከል ክርክር ይነሳል፡፡ ንጉሱና የካህናቱ አለቆች በተገኙበት አንድ እለት በጉባኤ ክርክሩ ተካሄደ፡፡ በመጨረሻም “እስጢፋኖሳውያን” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ተከራካሪዎች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠይቀው

አሻፈረን በማለታቸው ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ በሆነ በ38ኛው ቀን መጋቢት 10/1446 ዓ.ም ረዘም ላለ ጊዜ / ምናልባትም ለቀናት/ የቆየ ቦግ ያለ ብርሃን ከሰማይ ይወርዳል፡፡ የብርሃኑ መውረድ ለእስጢፋኖሳውያን ስህተተኛነት ለካህናቱ ደግሞ ትክክለኛነት ምስክር ነው በሚል ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ ብርሃን መውረድ የንጉሱ ዜና መዋእልም ያትታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ንጉሱ የስፍራውን ስም ደብረብርሃን /የብርሃን አምባ/ በማለት ሰይመውታል፡፡

አፄ ዘርአ ያአቆብ ከንግስና ዘመናቸው 14 አመት የሚሆነውን በደብረብርሃን ከተማ እንዳሳለፉና አብዛኛዎቹን የሃይማኖትና የፍልስፍና ድርሰቶቻቸውን የፃፉት በዚሁ ከተማ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዘመኑም ደብረብርሃን ከፍተኛ የትምህርት ማእከል የነበረች ሲሆን በንጉሱ ትእዛዝ በርካታ የሃይማኖት መፃህፍት የትርጉም ሥራ ተከናውኖባታል፡፡
አንጎለላ ና አንጎለላ ኪዳነ ምህረት
********************************
አንጎለላ ከተማ የምትገኘው ከደብረብርሃን ከተማ በስተምእራብ 10 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ በንጉስ ሳህለ ስላሴ /1805-1840/ ዓ.ም እንደተመሠረተች የሚነገርላት ሲሆን በሸዋም ሁለተኛዋ ከተማ ነበረች፡፡ ያለውጤት የቀረ ቢሆንም ንጉስ ሣህለ ስላሴ የውጭ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከእግንሊዝ /1834/ እና ከፈረንሳይ /1835 ዓ.ም/ መንግስታት ዲፕሎማቶች ጋር የንግድና የወዳጅነት ውል የተፈራረሙት በዚሁ በአንጎለላ ከተማ ነው፡፡የዳግማዊ ምኒሊክ የትውልድ ቦታ በሆነችው በዚችው በአንጎለላ ከተማ ታሪካዊቷ የአንጐለላ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ትገኛለች፡፡ በቤተክርስቲያኗ ዳግማዊ ምኒሊክ ክርስትና የተነሱባት

ከመሆኗ በተጨማሪ በአድዋ ጦርነት ህይወታቸውን ለአገራቸው መስዋእት ያደረጉት የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ገበየሁ አጽም በክብር አርፎበት ይገኛል፡፡ የጀግናው አጽም ከተቀበረበት የአድዋ የጦር አውድማ ከሰባት አመታት በኋላ እንዲመጣ ተደርጎ በክብር እንዲቀመጥ የተደረገውም አጼ ምኒሊክ ራሳቸው ባሰሩት ሳጥን መሆኑ ይነገራል፡፡

አድዋ ላይ ከወደቁት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆኑት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ “ጠላትን ስሸሽ ከሞትኩኝ አስከሬኔን እዚያው ቅበሩ፤ ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጬ ከሞትኩ ግን አስከሬኔን በሀገሬ ይቅበሩልኝ” ሲሉ አፄ ምኒልክን ቃል አስገብተዋቸው ነበር፡፡ የአድዋ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ገበየሁም እያዋጉ ጠላት ያለበት ድረስ በድፍረት ዘለቁ፡፡ ጠላት አናታቸውን በጥይት ሲነድል የፊት ጥርሳቸው ረግፎ በክብር ለአገራቸው ነፃነት ወደቁ፡፡ በሕይወት እያሉ-

“የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” የተባለላቸው ገበየሁ፤ አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አፅማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ፡፡ በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላም አጽሙ በአገራቸው በአንጎለላ ኪዳነምሕረት አረፈ፡፡
የአንጐለላ ከተማ ከፍተኛ የከተማነት እንቅስቃሴ የተካሄደባት ቦታ በመሆኗ ልዩ ዋጋ የሚሰጣቸው የስነ ህንፃ ቅርሶች ፍርስራሽ ይገኝባታል፡፡ ከ150 Aመታት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ የሚገመተው የንጉስ ሣህለ ስላሰ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተለይም በስሩ የሚገኘው አስገራሚው የቤተመንግስቱ የምድር ቤት አሠራር አይንን የሚማርክና የጥንት አባቶቻችንን የፈጠራ ውጤት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
***************
አንኮበር
*************
በ1733 ዓ.ም በሸዋው ነጋሲ በመርእድ አዝማች አምሀ እየሱስ /1733-1767 ዓ.ም/ የተመሰረተችው አንኮበር ከደብረብርሃን ምስራቃዊ አቅጣጫ 42 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

አንኮበር ከAጼ ይኩኖአምላክ /1262-1277 ዓ.ም/ ዘመን ጀምሮ ለኢትዮጰያ ነገስታት ማረፊያነት አገልግላለች፡፡ ኢፄ አምደጽዮን የድንኳን ከተማቸውን እንደተከሉባት ይነገራል፡፡ አፄ ልብነድንግል ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የባለወልድ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ጀምረው እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ የከተማነት ታሪኳ የጐላው ግን የሸዋ ስርወ መንግስት በመንዝ በማንሰራራት /1665-1881 ዓ.ም/ የመስፋፋት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደ እንጦጦ እስከዞረበትና በኋላም አዲስ አበባ እስከተቆረቆረችበት ጊዜ ድረስ በቀዝቃዛ አየሯ የምትታወቀው አንኮበር ለስድስት የሽዋ ነገሥታት በማእከልነት አገልግላለች፡፡ አንኮበር የሸዋ ነገስታት ቋሚ መናኸሪያ ለመሆን የበቃችው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስልጣን በያዙት ንጉስ ሳህለ ስላሴ / 1806-1840 ዓ.ም/ ነበር፡፡ ንጉሱ የእጅ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያበረታቱ በመሆኑ በርካታ የእደጥበብ ሥራዎች ይከናወኑባት ነበር፡፡ በቤተመንግስት የሚተዳደሩ ከ1000 በላይ አናጺዎችና ግንበኞች በተለይም ባሩድ ቀማሚዎች፣ የጦር መሣሪያ ሠራተኞችና አንጥረኞች በወቅቱ ነበሩባት፡፡

ዛሬ በአንኮበር ከአጼ ምኒሊክ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተጨማሪ በተለያየ ዘመን የተሰሩ አምስት አብያተ ክርስቲያናትና ዘመናዊ ሎጅ ይገኛሉ፡፡ እነሱም ፡- አንኮበር ጊዮርጊስ በ1733 ዓ.ም በአምሃ እየሱስ፣ አንኮበር ማርያም በ1767 ዓ.ም በአስፋው ወሰን፣ አንኮበር ሚካኤል በ1817 ዓ.ም እና አፈር ባይኔ ተክለሃይማኖት በ1821 ዓ.ም በንጉስ ሳህለስላሴ፣ አጼ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ በ1875 ዓ.ም የጋብቻ ሥነስርአታቸውን ሲፈጽሙ ቅዱስ ቁርባን የተቀበሉበት የመድሃኒአለም ቤተክርስቲያን በ1772ዓ.ም ሥራው ቢጀመርም በ1846 ዓ.ም በንጉስ ሃይለመለኮት የተሰሩ ናቸው፡፡
ረጅሙን ተራራ ተንተርሳ የምትገኘው የቁንዲ ከተማ ሌላዋ ታሪካዊ ቦታ ናት፡፡ ከተማዋ

የተመሰረተችው በመርእድ አዝማች ወሰን ሰገድ /1800-1805 ዓ.ም/ ነው፡፡ አንኮበር ለመድረስ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀር በምትገኘው ቁንዲ የሚገኘው ቤተመንግስት በግንብ የተከበበ እንደነበረ በዙሪያው የሚታየው ፍርስራሽ ያረጋግጣል፡፡ የቁንዲ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም የዚያን ዘመን የእደ ጥበብ ውጤት ያንፀባርቃል፡፡
***************
አልዩ አምባ
*************
የአንኮበር ታሪክ ሲዘከር የስምጥ ሸለቆ እካል የሆነችው የአልዩ አምባ ከተማና የአብዱል ረሱል የሙስሊም መቃብር ስፍራ አብረው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከአንኮበር ከተማ 12 ኪ/ሜ ያህል ቁልቁል ተወርዶ የምትገኘው አልዩ አምባ እንደ ሐረር በግንብ የተከበበች ስትሆን በምስራቅ፣ በደቡብና በምእራብ በሮች አሏት፡፡ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት የቀረጥ ኬላዎችና የንግድ ማእከል አንደኛዋ ነበረች፡፡ የፈረንሳይ ዲፕሎማት ሮቺ ሄሪኮርት እንደፃፈው ከ1500 እስከ 1700 የሚጠጉ ግመሎች የአገር ውስጥ ምርት ወደውጭ ያጓጉዙባት ነበር፡፡

በ1834 እና 1835 ዓ.ም በአገራችን መጀመሪያ የሆነው የቀረጥ ውል የተፈረመው በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው፡፡ በከተማዋ ከፐርሽያ / ኢራን/ ፣ ከህንድና ከአረብ አገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም ጎብኝዎች ጽፈውላታል፡፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመን የቀረጥ መስሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽ/ቤት ስራውን እንዲጀምር ተደርጎ ነበር፡፡ ስልክም ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ከእንጦጦ እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶለት ነበር፡፡ አልዩ አምባ የተዳከመችው የባቡር ሃዲድ በከተማዋ ማለፍ ባለመቻሉና ወደ ድሬዳዋ በመዛወሩ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዛሬ የአልዩ አምባ ገበያ አብዛኛዎቹን አርጎባዎች ይዞ የአፋርንና አማራ ብሔረሰቦችን ያገናኛል፡፡

********************************
ሳላይሽ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት
****************************
የአጼ ምኒሊክ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲሆን የሚገኘውም በሀገረ ማርያምና ከሰም ወረዳ ኮርማሽ ከተማ ነው፡፡ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ዋናውን መንገድ ተከትሎ 50 ኪ/ሜ ከተጓዙ በኋላ ወደግራ በመታጠፍ 13 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የኮርማሽ ከተማ ይደረሳል፡፡ ግምጃ ቤቶቹ በቁጥር 14 ናቸው፡፡ አሰራራቸው ደግሞ በእንቁላል ቅርጽ ነው፡፡ በ1890 ዓ.ም ከአድዋ ድል ማግስት ለጦር መሣሪያ ማከማቻነት ተብለው የተሰሩ ሲሆን የቦታው ስትራቴጂያዊ /ስልታዊ/ የተፈጥሮ አቀማመጥ የጐብኝን ቀልብ ይስባል፡፡ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቶቹ ቀደም ሲልም ለአፈንጋጭ ባለሥልጣናት እስር ቤት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከእስረኞቹ መካከልም ልጅ እያሱ ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ታሪካዊ ግንብ ቤቶች ለመንግስት መስሪያ ቤቶች በጽህፈት ቤትነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ይዘታቸውን ሳይለቁ የጥገና እድሳት ሥራ ተሠርቶላቸዋል፡፡
***********************************
የአቡኑ ከተማ ሰላ ድንጋይ
******************************
የአቡኑ ከተማ ሰላድንጋይ ከደብረብርሃን በስተሰሜን 72 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ለ38 አመታት የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ መንበረ ጵጵስናቸው በዚችው በሰላ ድንጋይ ነበር፡፡ በ1875 ዓ.ም በአቡነ ማቴዎስ የተሰራው የሰላድንጋይ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በ25 አመቱ በመብረቅ ቢፈርስም እንደገና በ1900 ዓ.ም በአጼ ምኒሊክ ልዩ ትእዛዝ ተሰርቶ ሚያዚያ 30 ንጉሱ ባሉበት በአቡኑ ተባርኳል፡፡ የቤተክርስቲያኑ ህንፃ የውስጥ አሰራር ውበት አይንን የሚማርክና የዘመኑን የህንፃ ሥራ ልዩ ችሎታ የሚመሰከር ነው፡፡ በውስጡም ከግብጽ ሀገር የመጣውን የአቡነ ማቴዎስ መቀመጫ ጨምሮ በርካታ የታሪክና የባህል ቅርሶች ይገኙበታል፡፡

ሰላድንጋይ የንጉስ ሳህለ ስላሴ የትውልድ ሥፍራም ናት፡፡ በእናታቸው በወይዘሮ ዘነበወርቅ እንደተሰራችና በስማቸውም የምትጠራው ሰገነት ከተሰራች 150 አመት አስቆጥራለች፡፡ ስላድንጋይ የአብዛኛዎቹ የሸዋ ነገስታት ሚስቶችና እቁባቶች መቀመጫ ስለነበረች የወይዘሮዎች ከተማ በመባልም ትታወቃለች፡፡

ከሰላድንጋይ አቅራቢ ከ1433 /1434/ ዓ/ም በአጼ ዘርአያቆብ የተተከለችው ደብረምጥማቅ ቤተክርስቲያንና ብዙ መነኮሳት የሚገኙባት የፃድቃኔ ማረያም ከፊል ዋሻ ደብር ይገኛል፡፡
*************************
ባልጭ አማኑኤል
************************
ባልጭ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የሚገኘው ከደብረብርሃን 260 ኪ/ሜ ርቆ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባልጭ ከተማ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ገላውዲዎስ ሲሆን አጼ ምኒሊክ በ1870ዎቹ አሳድሰውታል፡፡ በቅድስቱ ግድግዳ ላይ የተሳሉት ጥንታዊ የፈትል ስእሎች ከመንፈሳዊ መግለጫነት ባሻገር ደጃዝማች ምኒሊክ በልጅነታቸው በአጼ ቴዎድሮስ ሲማረኩ፣ በ1857 ዓ.ም ከመቅደላ ሲያመልጡና በኋላም በፍቼ

ከተማ ከአጼ ዮሐንስ /1864-1881 ዓ.ም/ ጋር ያካሄዱትን ስምምነት የሚገልጹ ናቸው፡፡ በመካነ ፈውስነቱ በአገራችን ስሙ እየገነነ የመጣው የሸንኮራ ዮሐንስ ፀበልም የሚገኘው ከባልጭ ከተማ የ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ ነው፡፡ ፀበሉ ቀደም ሲል በሽተኞችን ያድን እንደነበር ይነገር እንጅ ቀሳውስትና የፀበሉ አስተዳዳሪዎች ግን ከ1957 ዓ.ም ጀምሮ ዝናው እንደታወቀ ይናገራሉ፡፡ ፀበሉ የሚገኝበት አካባቢ ዳገታማና ቁልቁለት በመሆኑ ከአዲሱ ዩሐንስ ቤተክርስቲያን ህንፃ አጠገብ ሆኖ ሲመለከቱት የአካባቢውን አስደናቂ መልክአምድራዊ አቀማመጥና በተፈጥሮ ውበት የታደለውን የመስህብ ሥፍራ ማየት ያስደስታል፡፡
**************
ወፍ ዋሻ ደን
*************
ሸዋ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራዎች መካከል የወፍ ዋሻ ደን አንዱ ነው፡፡ ደኑ አምስት
ወረዳዎችን፡- ጣርማበር፣ ቀወትን፣ አንኮበርን፣ ላሎማማንና ጌራቀያን የሚያካልል ሲሆን 16925.5 ሄክታር የቆዳ ስፋት አለው፡፡ ደኑ ጎሽ ሜዳ፣ ወፍ ዋሻና ጓሳ በተባሉ የጉብኝት ሥፍራዎች የተከፋፈለ ነው፡፡ ጐሽ ሜዳ ከደብረብርሃን በ30 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በቀወት በኩል 12 ኪ/ሜ ጥርጊያ መንገድ አለው፡፡ ከአራት የማያንሱ ብርቅዬ አእዋፋት የሚገኙበት ጐሽሜዳ ከጭላዳ ዝንጀሮና ከምኒሊክ ድኩላ ከብርቅዬ እንስሳት በተጨማሪ አነር፣ ሚዳቋ፣ ጉሬዛና ሰስ ከመሳሰሉት ሌላ በአለም በየትኛውም ስፍራ የማትገኘው “አንኮበር ሴረን” ወፍ ብቸኛ መገኛም ነው፡፡

ከደብረብርሃን ወደ ደብረሲና 15 ኪ/ሜ በዋናው መንገድ ተሂዶና ወደ ምሥራቅ 14 ኪ/ሜ ገባ ብሎ እይታው የሚጀምረው ወፍ ዋሻ ደን በክረምት ወራት አእዋፋት ስለሚበዙበት የወፎች መሸሸጊያ /ዋሻ/ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከጎሽ ሜዳ ባልተለየ መልኩ ማራኪ ሲሆን በደብረሲና በኩል 7 ኪ/ሜ የክረምት ከበጋ ጥርጊያ መንገድ አለው፡፡ ጓሳ የሚገኘው በመሀል ሜዳ መዳረሻ ላይ ነው፡፡ ስያሜውን ያገኘውም በአካባቢው በብዛት ከሚበቅለው የጓሳ ሳር ነው፡፡ ቦታውን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ወርቃማው ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እፅዋትና ከአስራ አራት የማያንሱ በአገራችን ብቻ የሚገኙ አእዋፋት ያሉበት መሆኑ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ማራኪ መሆኑ ነው፡ ሰው ሰራሽ የሆነው የጣርማ በር ዋሻ የወፍ ዋሻ ደን አካል ነው፡፡ ከ1929 Eስከ 1932 ዓ.ም ባሉት አመታት በጣልያ የተሰሩት የጣርማ በር ዋሻዎች ሶስት ሲሆኑ ትልቁ 642 ሜትር ይረዝማል፡፡ የአገራችን ረጅሙ የመሬት ውስጥ መንገድ ከመሆኑም በተጨማሪ ሰሜን ኢትዮጵያን ከደቡብ ጋር የሚያገናኝ ዋና ጐዳና ነው፡፡
****************
የጐዜ መስጊድ
******************
የጐዜ መስጊድ ከደብረብርሃን ከተማ 93 ኪ/ሜ ርቃ ከምትገኘው የሸዋ ሮቢት ከተማ በስተምራብ በ15 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የጐዜ መስጊድ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የይፋት ስርወ መንግስት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ዘመን ከተሰሩት አርባ መስጊዶች ውስጥ አንዱና የመጨረሻው መሆኑ ይነገራል፡፡ ከ500 አመታት በላይ እድሜ እንዳለው የሚነገርለት ይህ መስጊድ አሰራሩ አራት ማእዘን ሲሆን ግድግዳውና ጣራው ባልተጠረቡ ድንጋዮች የተገነባ ነው፡፡ የድንጋዩን ክዳን የተሸከሙት አራት አግዳሚ የጣውላ ወራጆች ሲሆኑ ምሰሶዎቹ አራት ናቸው፡፡ መስጊዱ የአርጐባ መንደሮች በስተግርጌው አድርጎ ከኮረብታ ላይ ይገኛል፡፡ በዙሪያው ጥንታዊ የመቃበር ስፍራ፣ የድሮ ነዋሪዎች የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች እንዲሁም በውስጥ የቆዩ የሃይማኖቱ መሪዎች አራት ጦሮች አሉ፡፡

ቀደም ሲል በመስጊዱ ዙሪያ የአርጐባ ማህበረሰብ አባላት ይኖሩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ኮረብታውን ለቀው ከግርጌው መንደራቸውን መስርተው ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጅ ዛሬም ቢሆን መስጊዱ ዋነኛ የእምነት ቦታቸው ነው፡፡ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ይህ መስጊድ የአርጐባን ብሄረሰብና በአካባቢ ያለውን ውብ የተፈጥሮ መስህብ በስተግርጌው አድርጎ ሲታይ አይንን ይማርካል፡፡ ሸዋ ሮቢትም ዘወትር ማክሰኞና ቅዳሜ ሞቅ ደመቅ በሚለው ገበያዋ የአካባቢውን የአማራ፣ የአርጎባ የአፋርና ኦሮሞ ብሔረሰቦችን የምታገናኝ በመሆኗ ከጐዜ መስጊድ ጋር አጣምሮ በገበያው የሚታየውን ልዩ ትእይንት መመልከት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
*******************
የሙሽራ ድንጋዮች
*****************
በተለምዶ የሙሽራ ድንጋዮች በመባል የሚታወቁት ትክል ድንጋዮች ከአጣዬ ከተማ በምራብ በኩል 21 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ልዩ ስፍራው ገድሎ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛሉ፡፡ ገድሎ ሜዳ ንጉስ ምኒልክ በ1857 ዓ.ም ከመቅደላ እስር ቤት አምልጠው ሲሄዱ በምትካቸው በአጼ ቴዎድሮስ ተሹመው ከነበሩት በዛብህ ጋር ጦርነት ያደረጉበት ሥፍራ ነው፡፡ ጦርነቱም በአፄ ምኒልክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ገደሎ ሜዳ ቀደመ ሲል 44 ታቦታት የጥምቀት በዓልን የሚያከብሩበት ቦታ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ዛሬም በቅርብ የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት በሥፍራው በመሰብሰብ በዓልን ያከብራሉ ፡፡ ‹‹ሙሽራ ድንጋዮች›› በጋድሎ ሜዳ ምራባዊ ዳርቻ ላይ የሚገኙ የሠው ቅርጽ /መልክ/ ያላቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ፡፡ ትክል ድንጋዮቹ ቆመውና ካሉበት ሳይነሱ የሚገኙት 21፣ በሥፍራው ወድቀው የሚገኙ 2፣ ከስፍራው ተነስተው ገበሬዎች ለርሻው ድንበር መለያ የተጠቀሙባቸው 44 ናቸው ፡፡

የሙሽራ ድንጋዮች ስያሜቸውን ያገኙበት በአንድ ወቅት በመንገድ ላይ እያሉ ሙሽሮችና ሠርገኞች ባደረጉት ከልክ ያለፈ ጭፈራ እግዚአብሄርን በማሳዘናቸው ተረግመው ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ወደ ድንጋይነት ተቀይረው በዚያው እንደቀሩ ይነገራል፡፡

የሙሽራ ድንጋዮች ታሪካዊ አመጣጥ ከላይ በተገለጸው አኳኋን የተለየ ጥንታዊ ሰዎች ለአንድ አላማ ያቆሟቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ተብሎ ይታመናል ፡፡ ምንአልባትም ከአክሱም ዘመን በፊት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ የእደ ጥበብ ውጤት እንደሆነ ይገመታል፡፡ የሙሽራ ድንጋዮች በአብዛኛው ከደቡብ ኢትዮጵያ የጢያ ትክል ድንጋዮች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ እነዚህ ምስጢርን ያዘሉ የታሪካችን አሻራዎች ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙና ለተመልካች ደግሞ የሚያዝናኑ ናቸው.
***********************
የድንባሮ ማርያም
*************************
የድንባሮ ማርያም ቤተክርስቲያን በሰሜን ሸዋ ዞን በባሶና ወራና ወረዳ በባቄሎ ቀበሌ አስተዳደር ሥር ትገኛለች ፡፡ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ አርከስሉስ በተባሉት የሃይማኖት አባት በአፄ ናኦድ ዘመነ መንግስት እንደተመሰረተች የነገራል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ነገስታት ለዘመቻ ታቦታትን ይዘው ይጓዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አፄ ሚኒሊክ በ1888 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገራችን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የግፍ ወረራ ባካሄደበት ጊዜ ከንጉሱ ጋር በዘመቻው በግንባር ቀደም ከተጓዙት ታቦታት መካከል የድንባሮ ማርያም እንደነበረች ይነገራል፡፡ የአድዋ ድል መቶኛ ዓመት ‹‹በአድዋ ጦርነትና ድል የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ድርሻ›› በሚል ርእሰ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተዘጋጀው መጽሐፍ ብፁእ አቡነ ማቴዎስና አጼ ምኒልክ የድንባሮ ማርያምን ታቦት ይዘው 14 ጊዜ ዘመቻ አድርገው ድል ማግኘታቸውን ገልፀውታል፡፡ እናም ከንጉሱ የተበረከቱ በርካታ አክሊሎችና ንዋየ ቅድሳት በቤተ ክርስቲያኗ ይገኛሉ ፡፡
********************************
አብዱል ረሱል አብዱል ናስር
*******************************
አብዱል ረሱል ከአንኮበር ተራራ ሰንሰለት ግርጌ ከአልዩ አምባ ከተማ በስተደቡብ በግምት 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምራብ ወደ ምስራቅ የሚፈሰውን የደረቄ ወንዝን የሚያካልለው ጉብታ ላይ ይገኛል ፡፡ አካባቢው አብዱል ረሱል የሚለውን መጠሪያ ያገኘው አገሩን መጀመሪያ ካቀናው አብዱል ናስር ከሚባለው ሰው ሥም መሆኑ ይነገራል ፡፡አንዳንድ የታሪክ አሻራዎች አንደሚያመለክቱት አብዱል ረሱል ከ 1415 ዓ.ም. ጀምሮ የርጎባ ሕዝብ የወላስማ መሪዎቻቸውን ሽሽት ተከትለው ወደ ደቡብ ከመፍለሳቸው በፊት በይፋት ገነው በነበረበት / በ 1285-1415 ዓ.ም/ ዘመን እንደተመሰረተች ይታመናል ፡፡ 3000 የሚጠጉት የመቃብር ጡሉሎች /ድንጋዮች/ ያሉበትና ሁዳድ ተብሎ የሚጠራው ሥፍራ ከመንደሯ በስተምስራቅ ከ 1 እስከ 2 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል ፡፡

በዚህ የመቃብር ቦታ የከተማዋ መስራች የአብዱል ናስር መቃብርም አለ፡፡ የመቃብሮቹ ጡሉሎች የተለያየ ቅርጽ ያላቸውና ከአንድ ድንጋይ የተዘጋጁ ጠፍጣፋና በጥንቃቄ የተጠረቡ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ከ 1.5 እስከ 2 ሜትር ቁመትና ከ 25 እስከ 30 ሣ.ሜ. የሚደርስ ውፍረት አላቸው፡፡ የአብዱል ረሱል ከተማ ከ 13ኛው እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ለዘለቀው የባሪያ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆን አገልግላለች፡
**********************
ምሥሕለ ማርያም
**********************
ምስህለ ማርያም አጼ ብእደ ማርያም (1460-1470) እንደተቆረቆረችና እንደተሰየመች በዜና መዋእሉ ላይ ይገኛል፡፡ የቃሉ ትርጉም ‹‹ የማርያም መቀመጫ ›› ማለት ሲሆን በታሪክ እንደሚታወቀው ከ1262-1520 የነበሩት ነገስታት አገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩት በአብዛኛው ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በድንኳን ከተሞቻቸው እየተቀመጡ ስለነበር ምስህለ ማርያም የአጼ በእደ ማርያም የድንኳን ከተማቸው እንደነበረች ይገመታል፡፡ በዜና መዋእሉ መሠረት Aጼ በእደ ማርያም ቦታውን ምስሕለ ማርያም ብለው መሰየማቸውን ከመግለጻቸው ባሸገር ኖረውበት እንደሆነ አያብራራም ፡፡

ሆኖም በአፈ- ታሪክ አጼው ለአስርት ዓመታት እየተመላለሱ እንደኖሩባት ይነገራል፡፡ በ1991 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ ተመራማሪዎች የሚመራ የጥናት ቡድን በአካባቢው ያደረገው የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ የማሰባሰብ ሥራ የሚያበረታታና ጥናቱ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ፍንጮች ተገልጿል፡፡ ከ 1262-1520 ወዲህ ያለውን የታሪክ ዘመን የሚያሳዪ የመጀመሪያ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ሊሆኑ የሚችሉ ከሸክላ የተሰሩ ቁሳቁሶች በተደረገው ቁፋሮ ተገኝተዋል፡፡
*******************************************
የአፄ ሕዝብናኝ ቤተ- መንግሥት
************************************
የአጼ ሕዝብናኝ ቤተ- መንግሥት ፍርስራሽ ከደብረ ብርሃን ከተማ 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከእነዋሪ ከተማ በስተምራብ ደይ ጊዮርጊስ ቤተ- ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኛል ፡፡ አፄ ሕዝብናኝ የዳግማዊ አፄ ዳዊት ልጅ ሲሆኑ አገሪቱን ለ4 ዓመታት ከ 1422 -26 መርተዋል ፡፡ በዘመኑ የተሠራው ቤተ- መንግስታቸው በመካከለኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ግምትና ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የቤተ መንግስቱ ፍርስራሽ ህያው ምስክር በመሆን ለዘመናት ኖሮ በሥፍራው ይገኛል፡፡

ከመሬት በላይ የሚታየው የቤተ -መንግስቱ ፍርስራሽ አራት ደረጃዎች ሲኖሩት ርዝመቱ 14 ሜትር ስፋቱ 10 ሜትር ይሆናል ፡፡ የፍርስራሹ የውስጥ ግድግዳ የተሰራው ባልተጠረበ ድንጋይ ሲሆን የውጭው ግን የተጠረበና በሃረግ ያጌጠ ነው ፡፡ የፄ ሕዝብናኝ ቤተ- መንግስት ፍርስራሽ ከ13-15ኛው ክፍለ ዘመን ለነበረው የሕንጻ እደ ጥበብ ፍንጭ የሚሰጥና ለጥናትና ምርምር የሚጋብዝ ሆኖ ተገኝቷል ፡የደይ ጊዮርጊስ ቤተ- ክርስቲያን በዚያ ዘመን በንጉስ የተተከለ ሲሆን በአህመድ ግራኝና በጣሊያን ጊዜ በነበረው ጦርነት ዘመን የቃጠሎ አደጋ ቢደርስበትም በ 1953 ሕንጻው በአዲስ መልክ ተሠርቷል ፡:

ለተጨማሪ መረጃ መገናኛዉን ይከተሉ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.