ማሙሸት አማረ:- በኩራት በጽናትና በድፍረት የሚራመድ ታጋይ‏

ጥንት በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አንድ ንጉስ ስልጣኔን እነጠቃለሁ ብሎ ፈራ አሉ::እናም ጠንቋዮችን ሰበሰበ:: ጥያቄም ጠየቀ:: “ለምሆኑ ስልጣኔን የሚነጥቀኝ : ከኔ ብኋላ የሚነግሰዉ ማን ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀ:: ጠንቋዮቹም መለሱለት “ቀያይ : ቆንጆ: ቅንድባቸዉ ትልልቅ የሆኑ ሰዎችን ሰብስበህ ከሀገሪቱ ላይ አስወግዳቸዉ:: ምክንያቱም ከእነሱ አንዱ ይነግሳልና::” ሲሉ ምክር ሰጡት:: ንጉሱም እንደተመከረዉ አደረገ::

ሆኖም የጠንቋዮቹ ምክር ስላላረካዉ ወደ አንድ መለኩሴ ዘንድ ሄደ:: መለኩሴዉንም ተመሳሳይ ጥያቄ ጠየቃቸዉ:: መለኩሴዉ በንጉሱ ጥያቄ ተገረሙ:: እናም ንጉሱን ጥያቄ ጠዬቁት:: ” ለምሆኑ ካንተ ቀጥሎ እሚነግሰዉን ሰዉ ብታቀዉ ምን ታደርገዋለህ?” ሲሉ ጠዬቁት:: ንጉሱም መለሰ “አጠፋዋለኋ::” አላቸዉ::  መለኩሴዉ ፈገግ አሉ:: ፈገግ ብለዉም እንዲህ መለሱ “እግዚአብሄር የደበቀዉን አንተ ፈልገህ አታገኘዉም::ካንተ ብኋላ የሚነግሰዉ ሰዉም ከመንገስ አይቀርም::አንተ ብትፈልገዉም እግዚአብሄር ይጠብቀዋልና አታገኘዉም::”

አስገራሚዉ ነገር ታዲያ ንጉሱ አገር ምድሩን እያሰሰ ከኔ ብኋላ የሚነግሰዉን አገኘሁት በሚል ቀቢጸ ተስፋ ሰዎችን ሲያስጨርስ ንጉሱን ገልብጦ ስልጣን የያዘዉ አጠገቡ የነበረዉ የንጉሱ አሽከር/አገልጋይ/ ነበር:: መለኩሴዉ እንዳሉት እግዚአብሄር የደበቀዉን ንጉሱ ፈልጎ ሊያገኘዉ አልቻለምና:: ማን ተቃዋሚ ነዉ ወይም ማን ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል ብሎስ ማን ከኛ ብኋላ ሊነግስ ይችላል በሚል ታሳቢ ሁሉን ለማሰር መፋጠን እንደ ንጉሱ አይነት ሀሳባዊ ቀመር ዉስጥ መዉደቅ ነዉ:: ሰላማዊ ታጋዮችን ሁሉ በመጠርጠርና በመፍራት ማሰር ቀጥሎ ማን ሊነግስ ነዉ ብሎ እንደ ንጉሱ ሰዉኛ ስሌት ዉስጥ ተዘፍቆ አልወጣም ማለት ነዉ::

ሰሞኑን በጽኑ ሰላማዊ ታጋይነቱ የሚታወቀዉ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳትንት ማሙሸት አማረ ከላይ በተጠቀሰዉ ሀሳባዊ ስሌት ወደ እስር ቤት እንዲወረወር ተደርጓል::ማሙሸት አማረ በማያባራ የእስር ማዕበል ውስጥ በጽናት: በኩራት እና በድፍረት የሚራመድ ሰላማዊ ታጋይ መሆኑን ኢህአዴግ ጠንቅቆ ያዉቃል:: ማሙሸት አማረ በአላማዉ ላይ የማይደራደር: ትግልን ለሆዱ የማይሸጥ እና የቆመለት አላማን ብቻ በጽናት የሚያስተዉል ቀብራራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑን ኢህአዴግ በደንብ ያዉቃል:: ይሄ እዉቀት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም:: ማሙሸት አማረ ትግል የጀመረው በ1984 ዓም ሲሆን በ1980 ዎቹ ደብረብርሀን እስር ቤትን ሰብረህ እስረኛ አስመልጠሀል ተብሎ ሞት ተፈርዶበት ከረጅም እስር በኋላ የተለቀቀ ሰዉ ነዉ:: እንዲሁም በ1997 ዓም ከበርካታ የቅንጅት አመራሮች ጋር ይሙት በቃ ተብሎ ተፈርዶበት እንደማንኛውም የቅንጅት አመራር በይቅርታ የተፈታ ነዉ::

ማሙሸት አማረ ጥቅምት 28— 30 2007 ዓም መኢአድ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከ483 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ውስጥ 477 አባላት በሙሉ ድምጻቸዉ የመኢአድ ፕሬዝደንት አድርገዉ የመረጡት ወጣትና ቆራጥ ታጋይ ነበር:: ሆኖም በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠዉ አመራር ተባሮ ለአቶ አበባዉ (6 ሰዎች ለደገፉት ሰዉዬ) መኢአድ ተላልፎ እንዲሰጥ ሲደረግ ( በምርጫ ቦርድ ውሳኔ) ማሙሸት አማረ የመኢአድ ሰላማዊ ትግል በማይናወጽ መሰረት ላይ ይቆም ዘንድ ምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መስርቶ በፍርድቤት የክርክር ሂደት ላይ ነበር:: ማሙሸት አማረ በድል ወቅት እዉኝ እዉኝ የማይል : በመከራም ወቅት በጽናት የሚቆም ሰዉ ነዉና የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እንደ ጉም ተበትኖ እንዳይጠፋ

የሰላማዊ ትግል እርምጃ ብሎም እራሱን የፍትህ ሂደቱን በጽኑ መሰረት ላይ ቆሞ ለመፈተን የተጠና እርምጃ ወስዶ ነበር::በተለይም ምርጫ ቦርድን በመክሰስ የምርጫ ቦርድን ስህተት ዉሳኔ ለመቀልበስ እልህ አስጨራሽ ክርክር ዉስጥ ገብቶ ነበር::  ሆኖም ኢህአዴግ ሰላማዊ ታጋይ በሙሉ ይታሰር የሚል መፈክር ያወጣ በሚመስል ሁኔታ ሁሉንም ወገን ማሰር መሰረታዊ አቋሙ አድርጎ ተነስቷልና ማሙሸት አማረንም ወደ እስር ቤት ያለ ፍርድቤት ዉሳኔ አንቆ ከቶታል::  የማሙሸት አማረን እስር ልዩ የሚያደርገዉ ግን ህጉን አክብሮ በፍርድቤት ክርክር እያደረገ የተነጠቀዉን የሰላማዊ ትግል ፓርቲ ለማስመለስ የገዥዉን እስትንፋስ እያደመጠ የሚሰራዉን ምርጫ ቦርድን እየሞገተ ባለበት ወቅት መሆኑ ነዉ::

የሆኖ ሆኖ ግን ይሄንኑ የክስ ሂደት ቀሪዎቹ የመኢአድ አባላት እስከ ሰበር ድረስ ይዘዉት እንደሚሄዱና ምርጫ ቦርድ ላይ ፍርድ ቤት ምን እንደሚወስን ለማዬት ብሎም ፍርድ ቤቱን እንደ ተቋም በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደትና ጥያቄ ሊፈትኑት እንደሚችሉ ይጠበቃል::  ማሙሸት አማረ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ማበብ በጽናት የታገለ: በሰላማዊ ትግል ላይ ጽኑ አቋም ያለዉ: በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል የተዛባ የጥላቻ መንፈስ እንዳይፈጠር በማያወላዉል አቋም የታገለ ሰዉ ነዉ:: በርካታ ጋዜጠኞች: የልዩ ልዩ ፓርቲ አመራሮች እና የመኢአድ አባላት ደጋግመዉ የከፈሉትን የጀግንነት ዋጋ ሊከፍል ለስንተኛ ጊዜ ማሙሸት አማረ ወደ እስር ቤት ወርዷል:: የማያባራ: የማያቆም: መነሻና መድረሻ የሌለዉ እስር::

በዚህ ሁሉ የእስር ማዕበል ዉስጥ እየተራመዱ ሰላማዊ ትግል መታገል በጣም አስደናቂ ነዉ:: ያዉም ህዝቡ የሚከፈልለትን ዋጋ በሾርኒ በሚያይበት ወቅት:: አስደናቂነቱን ዉስብስብና የጸነነ የሚያደገዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰዉ ወርቃማዎቹን ታጋዮቹን እና አስመሳዎቹን ታጋዮች ለማወቅ የሚያደርገዉ ጥረት ብሎም ለወርቃማዎቹ ታጋዮች የሚያደርገዉ ድጋፍ ኢምንት መሆኑ ነዉ::የማስታወቂያ ጀግኖችን እና እዉነተኛ ጀግኖችን ለመለዬት ተቋም ያልገነባ ህዝብ መሃል ትግል እንደማድረግ ምን ከባድ ነገር አለ? እናም የመለኩሴዉ ምክር እዚህ ልብ ሊባል ይገባል:: “እግዚአብሄር የደበቀዉን አንተ ፈልገህ አታገኘዉም::ካንተ ብኋላ የሚነግሰዉ ሰዉም ከመንገስ አይቀርም::አንተ ብትፈልገዉም እግዚአብሄር ይጠብቀዋልና አታገኘዉም::” የሚለዉን አባባል ገዥዎቻችን ልብ ብለዉ ቢያስተዉሉት ጥሩ ነዉ::

ሰላማዊ ታጋይን ሁሉ ገና ለገና ከኔ ቀጥሎ ይነግሳል እያሉ ሁሉን ማሳደድና ማሰር መካር ማጣት ነዉ:: እግዚአብሄር የቀጸበዉ ቀን ከደረሰ እግዚአብሄር ለደበቀዉ ወገን ስልጣኑ መተላለፉ አይቀርምና::  እናም እንመክራለን እንዲህ ስንል :- ” ሰላማዊ ታጋዮችን አትንኳቸዉ:: በሰላማዊ የትግል ሂደት የሚገነባዉ ዲሞክራሲያዊ እሴት ሰፊ መሰረት ላይ የሚቆምና ለሁሉም ወገን ፍቱን መደሃኒት ነዉና::ሰላማዊዉ መንገድ ሲታጠር የሚወለደዉ የትግል ስልት ግን ለሁሉም ወገን የሳት ላንቃ ያለዉ ይሆናል:: “


ሸንቁት አየለ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.